Fana: At a Speed of Life!

የአንድን ቻይናዊ ሕይወት በማጥፋት ወደ ኬንያ የሸሹ ተጠርጣሪዎች ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጡ

አዲ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የአንድን ቻይናዊ ሕይወት በማጥፋት ወደ ኬንያ ሸሽተው የነበሩ ተጠርጣሪዎች ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ብሔራዊ ኢንተርፖል ተላልፈው ተሰጡ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው መስቀል ፍላወር ቶሎሳ ለገሰ ሆቴል 5ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የቻይና ሬስቶራንት ውስጥ ፉ ሁይ የተባለውን ቻይናዊ ሕይወት በማጥፋት ወንጀል ተጠርጥረው ሲፈለጉ የነበሩ አራት ቻይናውያን በኬንያ በቁጥጥር ስር ውለው ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ብሔራዊ ኢንተርፖል ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንተርፖል ዳይሬክተር ኮማንደር ፀጋዬ ሀይሌ እንደተናገሩት ÷ ሁዋንግ ዥፔንግ ፣ ሊቭ ጄ ፣ ዋንግ ሚንግ እና ቻ ኦ ፉ ሲዛኦንግ የተባሉት አራት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን ከፈፀሙ በኋላ ወደ ኬንያ አምልጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንተርፖልም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ምርመራውን በፍጥነት በማካሄድ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ዓለም አቀፍ የኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያ አውጥቶባቸው ሲፈለጉ እንደነበር ነው ዳይሬክተሩ ያወሱት፡፡

ለ24 ሰዓት በተደረገ የመረጃ ልውውጥ ኬንያ መግባታቸው በመረጋገጡ÷ ከኬንያ ብሔራዊ ኢንተርፖል ጋር በጥምረት በመስራት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ኮማንደር ፀጋዬ፡፡

አራቱም ቻይናውያን ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ወደ ተጠረጠሩበት ኢትዮጵያ ገብተው ምርመራ እንዲጣራባቸው ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል ማለታቸውምን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ማንኛውም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከሕግ ማምለጥም ሆነ መደበቅ እንደማይችል በዓለም አቀፉ የፖሊስ ኀብረት ኢንተርፖል ተፈልጎ ሕግ ፊት የሚቀርብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.