Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት ሰላማዊ አፍሪካን ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት አፍሪካን ከጦር መሳሪያ ድምጽ ነፃ ለማድረግ በአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የተጀመረው ስራ እውን እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

10ኛው የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት የጋራ ስብሰባ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በጋራ ስብሰባው ላይም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደርለይን እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ተሳትፈዋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደርለይን በመክፈቻው ላይ፥ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ እድገት መረጋገጥ በቅድሚያ ሰላማዊ አፍሪካን መገንባት የግድ ይላል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የተኩስ ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን እውን ለማድረግ ተስማምተው ወደ ስራ መግባታቸውን ያደነቁት ፕሬዚደንቷ ፥ “የአውሮፓ ህብረት የተጀመረው ስራ እውን እንዲሆን የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል” ሲሉም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ከአሁን በፊት በሰላምና ፀጥታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ አፍሪካውያን አሁን እየጀመሩት ያለው የነፃ የንግድ ቀጣና ስርዓት መጠናከር እንዳለበት የአውሮፓ ህብረትም ሊደግፈው የሚገባ እንቅስቃሴ እንደሆነ አመልክተዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይና የሁለቱንም ህብረቶች አባሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲጎለብት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት በበኩላቸው “አሁን እየታዩ ላሉት የአፍሪካዊያን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት አለም ዓቀፋዊ የባለብዙ ዘርፍ ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልገናል” ብለዋል።

አፍሪካዊያን በአሁኑ ወቅት ከመሳሪያ ድምጽ ነፃ የሆነ አህጉር ለመገንባት አንድ የሆነ የፖለቲካ አቋም ይዘው እየሰሩ መሆናቸውንና ለውጥ እየመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአህጉሩ ኢንቨስትመንትና ንግድን ለማጠናከር የሚያስችል ነፃ የንግድ ስርአት ተግባራዊ ማድረግ እንደጀመሩ መግለፃቸውንም የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የሚገኙት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደርለይን ከስብሰባው ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተገኝተው የአየር መንገዱን የአቪየሽን አካዳሚና የተለያ የስራ እንቅስቃሴዎች ጎብኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.