Fana: At a Speed of Life!

የአየር መንገዱ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር ለኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ግምቱ 1 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የህክምና ግብዓት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር ለኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ግምቱ 1 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የህክምና ግብዓት ድጋፍ አደረጉ፡፡

የማህበሩ ሊቀመንበር ካፒቴን በረከት አባተ 400 የቀዶ ጥገና አልባሳትና የፕላስቲክ ቡትስ ጫማዎች፣ አይፓድና ላፕቶፖችን ጨምሮ ሌሎች የህክምና ግብዓቶችን ለሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶክተር ያሬድ አግደው አስረክበዋል፡፡

ካፒቴን በረከት ፓይለቶች የመጀመሪያውን ጫና ተቀባዮች ሆነው ኢኮኖሚው እንዳይዳከም እየሰሩ እንደሆነ አንስተው የህክምና ቁሳቁሶችን በየሀገራቱ በማከፋፈልም በትርፍ ሰአታቸው ጭምር በመስራት በሙያቸው በማገልገል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

እንዲሁም ከእነሱ በላይ ተጋላጭ ሆነው በማገልገል ላይ ያሉትን የህክምና ባለሙያዎችን መደገፍ አለብን በሚል ድጋፉን ለማድረግ መነሳሳታቸውን ተናግረዋል።

አቅም ያላቸው ሌሎች ማህበራትም ይህን መሰል ባለሙያዎችን ታሳቢ ያደረጉ ድጋፎች እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶክተር ያሬድ አግደው በበኩላቸው ለድጋፉ ማህበሩን በማመስገን፥ ወረርሽኙ በተስፋፋ ቁጥር የህክምና ባለሙያዎች እንዲጠቀሙ የሚመከሩ አልባሳት ላይ ለውጥ እየተደረገና ጥብቅ እየሆነ በመሄዱ ከመንግስት ባሻገር አቅም ያላቸው ኢትዮጵያዊ ማህበራት ሁሉ መሰል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከተመሰረተ 50 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ወስዶ ሲሰራ የቆየና እየሰራ የሚገኝ ማህበር ነው።

በአክሱማዊት ገብረህይወት

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.