Fana: At a Speed of Life!

የአይቲ ባለሙያው የግንባታ ስራ መቆጣጠርያ ሶፍትዌር ፈጠረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ ከተማ ነዋሪ የሆነው የአይቲ ባለሙያ ታምራት ታንጋ የግንባታ ስራዎችን ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል ‘አውቶሜትድ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም’ የተሰኘ ሶፍትዌር ፈጠረ።
ሶፍትዌሩ የግንባታ ሂደት የደረሰበትን ደረጃና የክፍያ ሁኔታን የሚያመላክት መሆኑን÷ የፈጠራው ባለቤት ታምራት ታንጋ ለኢዜአ ተናግሯል፡፡
ሶፍትዌሩ ግንባታው መቼ ተጀመረ፣ ስንት ጊዜ ሆነው፣ ያለበት ደረጃና የክፍያ ሁኔታ ምን ይመስላል? የመሳሰሉትን መረጃዎችን በተተነተነ መልኩ ሙሉ የግንባታ መረጃዎችን ማቅረብ ያስችላልም ተብሏል፡፡
የዘገዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለምን እንደዘገዩ ለመለየትና የግንባታ ደረጃውና የክፍያ ሁኔታው ካልተመጣጠነ መጠየቅ እንዲችሉ እንደሚግዝም ነው የፈጠራው ባለቤት የተናገረው፡፡
ሶፍተዌሩ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በእንግሊዝኛ የሚሰራ ሲሆን የግንባታ ተቋማት በዌብ ሊንኩ አማካኝነት የሚጠቀሙበት እንደሆነም ተናግሯል።
“ሶፍትዌሩ ስለ ግንባታ ስራው የንዑስ ስራ የጨረታ አወጣጥ ሁኔታ፣ የተፈጠረ የስራ እድል፣ ያጋጠመ ችግር፣ በተመለከተም የተሟላ የበይነ መረብ ሪፖርት ይሰጣል” ብሏል።
የጅማ ዞን የኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ናስር ሙሳ በበኩላቸው÷ “ሶፍትዌሩ በየጊዜው የሚገባለትን መረጃ በማቀናጀትና በመተንተን የተጣራ መረጃን ለሚመለከተው አካል ያቀርባል” ብለዋል።
በዘርፉ ያሉ ችግሮችን እንደሚያስቀር እምነት እንዳላቸው ገልጸው÷ ሶፍትዌሩ ለመቆጣጠር የተፈለገው የቦታ ክልል ውስጥ ያለን ማንኛውም የግንባታ ስራ ጊዜና ጉልበት ሳያባክን በቀላሉ መከታተል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ድርጅቶች፣ ማህበራትና ግለሰቦች የሚያወጡትን የተለያዩ የግንባታ የሙያ ፈቃድ በመለየት የሚያሳውቅና የሚያጋልጥ በመሆኑ ወጥ አሰራር እንዲሰፍን የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።
ለሶፍትዌሩ የፈጠራ ባለቤት የኢትዮጵያ አምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት መብት የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.