Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ835 ሚሊዮን ብር ወጪ ብር የሚገነባው የአዲስ አበባ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ በይፋ ተጀመረ።
 
በቻይናው የኮሙዩኒኬሽን እና ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲ ሲ ሲ ሲ) የሚከናወነውን ይህን ግንባታ የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ በይፋ አስጀምረውታል።
 
ማዕከሉ የትራፊክ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የትራፊክ መብራቶችን የቆይታ ጊዜ እንደ ትራፊክ ፍሰቱ መጠን የመቀያይርና ልዩ ልዩ የትራፊክ ፍሰት ማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ስራም ይከናወንበታል ተብሏል።
 
በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የመንገዶችን የትራፊክ ሁኔታ ቀድመው እንዲያውቁና አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ መረጃ የመስጠት፣ የትራፊክ ህጎችን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን የመለየት እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት፣ የአደጋ እና የደህንነት መረጃዎች ወደሚመለከታቸው ልዩ ልዩ ተቋማት በጊዜው እንዲተላለፉ ማድረግ ያስችላልም ነው የተባለው።
 
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ ፍሰት ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
 
የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከሉ ከመሬት በታች አራት ወለሎች ሲኖሩት፥ ከትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል በተጨማሪ መረጃ ማደራጃ ክፍሎች፣ የወንጀልና የአደጋ መከላከያ መረጃ ቢሮዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ያካትታል።
 
ማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎች እና መሰረተ ልማቶች የሚሟሉለት ሲሆን በ18 ወራት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሏል።
 
ከቅርብ ጊዜ በኋላ በከተማዋ በተመረጡ ቦታዎች የክፍያ መንገዶች ስራ እንደሚጀምሩም በስነ ስርዓቱ ላይ ኢ/ር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።
 
ከክፍያ መንገዶች የሚገኘው ገቢም የህዝብ ትራንስፖርትን ዘመናዊ ማድረግ ላይ ይውላል።
 
ሌላው በዕለቱ ግንባታው የተጀመረው በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በአንድ ማዕከል ለማሰባሰብ የሚረዳ ህንጻ ግንባታንም አስጀምረዋል።
 
የህንጻው ግንባታ የአገልግሎት አሰጣጡ ህብረተሰቡን በሚመጥን መልኩ በአንድ ቦታ ለመስጠት የሚረዳ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚያወጣውን የህንጻ ኪራይ ወጪ የሚያስቀር ይሆናል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.