Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴን አፈጉባኤ አድርጎ ሾመ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 8ኛ አመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
ምክር ቤቱ ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ አድርጎ ሾሟል።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ የከተማዋን ሩብ አመት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርቱም በሩብ አመቱ አመራሩን ብቁ የማድረግ፣ የመሠረተ ልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል ።
በበጀት አመቱ ሩብ አመት ለ42 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ43 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር መቻሉንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈም የከተማ አስተዳደሩ በሩብ አመቱ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 10 ነጥብ 87 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 9 ነጥብ 99 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉም ተገልጿል።
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ428 ሚሊየን ብር ብልጫ አለው ተብሏል።
በ40/60 እና በ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ወጥቶባቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይተላለፉ የቆዩ ቤቶችን ለባለ እድለኞች የማስረከብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በሰጡት ማብራሪያ በመዲናወ የንግድ ስርአቱን ከህገወጥ እና ኢ ፍትሃዊ አሰራር ለመከላከል በ3 ሺህ 356 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል፡፡

በምክር ቤቱ የዛሬ ውሎ በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ተጨማሪ ክፍለ ከተማ ለመመስረት የቀረበ ሃሳብ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል፡፡

አዲስ ይመሰረታል የተባለ ክፍለ ከተማ “ለሚ ኩራ” ተብሎ የሚጠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

አዲሱ ክፍለ ከተማ በምክር ቤት ከጸደቀ በአዲስ አበባ የሚገኙ ክፍለ ከተሞች ቁጥር ወደ 11 የሚያድግ ይሆናል፡፡

በከተማዋ አሁን ላይ 10 ክፍለ ከተሞች እና 116 ወረዳዎች እንደሚገኙ ይታወቃል።

ምክትል ከንቲባዋ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍና አገልግሎቱን ለማሻሻል አሰራርን በማሻሻል ተጨማሪ 560 አውቶብሶችን በኪራይ ወደ ስምሪት በማስገባት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን አውስተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም 3 ሺህ ዘመናዊ የከተማ አውቶብሶች ግዢ ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መንገዶች ግንባታ እንዲሁም ተጨማሪ የፓርኪንግ ቦታዎችን በማዘጋጀት የትራንስፖርት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በትምህርት ዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ትምህርት ለማስጀመር በተደረጉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ከ2 ሺህ 300 በላይ ተጨማሪ ክፍሎችን እና የ289 የምገባ አዳራሾች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት ሆስፒታል ህክምና ለሚያገኙ የኩላሊት ህሙማን የ2013 ዓ.ም ወጪያቸው ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ መሸፈኑንም አውስተዋል፡፡

ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞም ዕጣ ወጥቶባቸው ርክክብ ሳይደረግባቸው የቆዩ ቤቶችን ለባለ እድለኞች የማስተላለፍ እንዲሁም ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የካሳና የምትክ ቦታ ጥያቄ ትክክለኛነት በማረጋገጥ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑት የማስተላለፍ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም በአጭር ጊዜ ውስጥ 100 ሺህ ቤቶችን ከአጋር ድርጅቶች እንዲሁም 26 ሺህ ቤቶችን በባንክ ብድር አገልግሎት ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመጥቀስም ፍላጎትና አቅም ላላቸው ተመዝጋቢዎች ተደራጅተው እንዲገነቡ አማራጭ መዘርጋቱንም ነው ያነሱት፡፡

የነዋሪውን ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ከወረዳ እስከ ማዕከል የሰላም ምክር ቤት እንዲቋቋም እና የመንግስት ጸጥታ ምክር ቤት ተጠናክሮ እንዲሰራ የጸጥታ መዋቅር የሪፎርም ስራ ውጤታማ እንዲሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታልም ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.