Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ተጨማሪ 500 ሚሊየን ብር ለሪቮልቪንግ ፈንድ ፈቀደ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የመሰረታዊ ፍጆታ ምርት ለማቅረብ እና የእሕል የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ከዚህ ቀደም ካደረገው ብድር በተጨማሪ የ500 ሚሊየን ብር ለሪቮልቪንግ ፈንድ ፈቀደ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ሕዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም በአንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ከውሳኔዎቹ መካከል፡-

1. ሆፕ ፎር ችልድረን ኦርጋናይዜሽን አውስትራሊያ ሊሚትድ የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 1 ክልል ውስጥ በ600 ሚሊየን ብር የመሬት አጠቃቀሙ ባለ ብዙ አገልግሎት የሆነ ቦታ ላይ ወላጅ አልባ እና ደጋፊ ለሌላቸው ሕጻናት የልህቀት ማእከል ለመገንባት በመሬት ልማትና አስተዳደር የቀረበውን የውሳኔ መነሻ ተቋሙ ስራውን አጠናቆ ወደ ተግባር ሲገባ የሚሰጠውን አገራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀው ቦታ ከዚህ ቀደም መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት በሚስተናገዱበት መሰረት እንዲስተናገዱ ካቢኔው ውሳኔ አሳልፏል ፡፡

2. በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በዝናብ እጥረት ምክንያት በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የ100 ሚሊየን ብር የአይነት ድጋፍ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህ መሰረት የ50 ሚሊየን ብር ለሶማሌ ክልል እና የ50 ሚሊየን ብር ለቦረና ዞን የአይነት ድጋፍ እንዲደረግ እና ይህን ተግባር የሚያስፈጽሙ የካቢኔ አባላት ኮሚቴ ሰይሟል፡፡

3. የከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የመሰረታዊ የፍጆታ እቃ የሚውል የሸማቾች የሕብረት ስራ ማኅበራት ያለባቸውን የካፒታል እጥረት ለመቅረፍ ፣ የመሰረታዊ ፍጆታ ምርት ለማቅረብ እና የእሕል የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ይቻል ዘንድ ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም ካደረገው 500 ሚሊየን ብር ብድር ድጎማ በተጨማሪ ለሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች የግብርና ምርቶች የሚያቀርቡበት ብድር ማቅረብ አስፈላጊ በመሆኑ ለጤፍ እና ለስንዴ ግዢ የሚውል 500 ሚሊየን ብር ለሪቮልቪንግ ፈንድ የፈቀደ ሲሆን የግዢ ሂደቱም የሸማቾች ሕብረት ስራ ማኀበራት ግዢውን በቀጥታ ከአምራች መሰረታዊ ማኅበራት እንዲፈጽሙ ካቢኔው ወስኗል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.