Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ ጉዳይ ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑ አነጋጋሪ ሆኖ በሰነበተው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ5ኛ ዓመት ተማሪ ከሆነው ቢኒያም ኢሳያስ ጋር በተያያዘ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ዩኒቨርሲቲው ተማሪ ኢሳያስ የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለ የግራ እጁ ላይ በተፈጥሮ የአካል ጉዳት ያለበት መሆኑ በመምህራን ከተለየ በኋላ ይህ ጉዳት በህክምና ትምህርቱ ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዲታይ ወደ ዲን ጽህፈት ቤት መርቶት እንደነበር አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮሌጁ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ላለፉት ስምንት ወራት ጉዳዩን ሲመለከቱት መቆየታቸውም ተገልጿል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው እና የጤና ሳይንስ ኮሌጁ የተማሪ ቢኒያምን ጉዳይ እንደ ተማሪ፣ እንደ አካል ጉዳተኛ እና የህሙማንን ጉዳይ በየዘርፉ ለይተው ምክክር ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም ደነቀ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን በማሳተፍ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፥ መሰረታዊ በሆኑ የህክምና ተቋማት ላይ ቴክኒካል የሆኑ አሰራሮችን መመልከት መቻሉንም አስረድተዋል።

ባገኘው አሰራርም አንድ የህክምና ባለሙያ በመሠረታዊነት መስጠት ያለበትን የህክምና እርዳታ የሚያሟላውን መስፈርት በተመለከተም፥ ተማሪ ቢኒያም በዩኒቨርሲቲው ከሚሰጡ ስምንት የቅድመ ምረቃ ትምህርቶች አምስቱን ለመማር እና ለወደፊት ሙያውን ለመተግበር እንደሚቸገር ከስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

ነገር ግን በሌሎች የትምህርት አይነቶች ትምህርቱን መቀጠል እንደሚችል አብራርተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተሰጠ ውሳኔም ዩኒቨርሲቲው ችግሩን በወቅቱ ለይቶ አማራጮችን ባለመውሰዱ እና በተማሪው ላይ ለደረሰው የሞራል ጉዳት ሃላፊነቱን እንደሚወስድም ገልጸዋል።

በቀጣይ ተማሪ ቢኒያም ትምህርቱን በሚከታተልበት ሂደት ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

በቆንጅት ዘውዴ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.