Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የስነ ምግባር ጉድለት በተገኘባቸው 29 ሰራተኞች ላይ ርምጃ መውሰዱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የስነ-ምግባር ጉድለት በተገኘባቸው 29 ሰራተኞች ላይ ርምጃ መውሰዱን ገለጸ።

ቢሮው የመጀመሪያ ስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ከክፍለ ከተማ የገቢዎች ጽህፈት ቤቶች ከተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በውይይቱ እንዳሉት፤ በቀጣይ በባለሙያና በአመራር ስነ-ምግባር ላይ በትኩረት ይሰራል።

ቢሮው ከግብር ከፋዩ ጋር ያለው ግንኙነት መሻሻሉ በባለሙያዎችና በአመራሮች ላይ ይታዩ የነበሩ የስነ-ምግባር ጉድለቶች ለማረም እንዳገዘው ገልጸዋል።

ከግብር ከፋዩ የሚመጡ ጥቆማዎችንና መረጃዎችን ትክክለኛነት በማጥራት የስነ-ምግባር ጉድለት የሚገኝባቸው ባለሙዎችና አመራሮች ላይ ርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

በዚህም በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ የስነ-ምግባር ጉድለት በተገኘባቸው 29 ባለሙያዎች ላይ ከከባድ የዲስፕሊን ጥፋት ቅጣት ከስራ እስከማሰናበት የደረሰ ርምጃ መወሰዱን አቶ ሺሰማ አመልክተዋል።

በሌሎች አገሮች ከፍተኛ ግብር ከሚሰበሰብበት የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ የሚሰበሰበው ግብር አነስተኛ እንደሆነ የተናገሩት የቢሮው ሃላፊ፤ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር የማረም ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታትና ገቢውን ለማሳደግ ግንዛቤ የማሳደግና ህግን የማስከበር ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በመጀመሪያው ስድስት ወር በከተማ አስተዳደሩ የተሻለ አፈጻጸም ካስመዘገቡት መካከል አንዱ የሆነው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማህተመ አብርሃ በግብር አሰባሰብ ሂደት ለውጥ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ነገር ግን አሁንም የተጨማሪ እሴት ታክስ አሰባሰብ ችግር ውስጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም የደረሰኝ አቆራረጥ፣ ህገወጥ ደረሰኝ መጠቀምና ተያያዥ ችግር እንዳለ አመልክተዋል።

ወደፊትም ገቢውን ለማሳደግ ቢሮው በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ በሠራተኛ አቅም ግንባታ፣ በታክስ ህግ ማስከበር፣ በመረጃና ኢንተሊጀንስ ስራው ላይ አጠናክሮ እንደሚሰራ ተነግሯል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.