Fana: At a Speed of Life!

የአድዋ ድል አባቶቻችን እና አያቶቻችን በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በአንድነት እና በመዋደድ ያስመዘገቡት የድል ክብረ ወሰን ነው -ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ 8ኛ ዙር የአድዋ ተጓዦችን ስንቅ በመስጠት ሸኝተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ በሽኝት መርሀ ግብሩ ላይ ÷ የአድዋ ድል አባቶቻችን እና አያቶቻችን በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በአንድነት እና በመዋደድ ያስመዘገቡት የድል ክብረ ወሰን ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን፣ ህዝቦቿን እና መሪዎቿን የናቁ ሁሉ እንደሚዋረዱ የሚናገር ሕያው የታሪክ መጽሐፍ ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች÷ እንደ አባቶቻችን እና አያቶቻችን ይቺን ውድ አገር አንድ ሆኖ ማስከበር እና ማሻገርን አንርሳ ብለዋል፡፡
ይህ የአድዋ የታሪክ መጽሐፍ ትላንት፣ዛሬም ነገም እውነቱን እንደያዘ ይዘልቃል ከዚህ ታሪክ መማር ያለባቸው ባዕዳን እና ወራሪ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ እኛም ኢትጵያዊያን ከገዛ ታሪካችን መማር አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ወይዘሮ አዳነች አያይዘውም የአድዋ ድል በጠመንጃ ብቻ በመታገዝ የተገኘ ድል አይደለምም ብለዋል፡፡
የበርካቶችን ልብ በማሸነፍ የተገኘ የእውነተኞች ጭምር ድል መሆኑን የገለጹት ምክትል ክንቲባዋ ዛሬም ኢትዮጵያ እውነትን ስለያዘች ታሸንፋለች ሲሉ ገልጸዋል።
አባት አያቶቻችን በአድዋ የዘመቱት የሀገሪቱን ውስጣዊ አንድነት በደም አስተሳስረው በጋራ ጠላት ላይ በመዝመት የጋራ አገር ለመገንባት ጭምር ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች÷ ያሉንን ልዩነቶች በማቆየት ይሄን ክፉ ቀን ለማለፍ ዳር እስከ ዳር እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት እንድንቆም ሲሉ ይህንንም የአድዋ ተጓዦች በሄዱበት መንገድ ሁሉ እንዲያደርሱ የአደራ መልዕከት አስተላልፈዋል፡፡
የአፍሪካ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ በእግር ተጓዥ የሆኑትን ጀግኖች በክብር ስንሸኛችሁ በጉዟችሁ መዳረሻ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ፍቅራችሁን ለሀገርና ለወገን ወዳዱ እንግዳ ተቀባዩ ህዝባችን እያሳያችሁ የሴቶች ተጓዦች ተምሳሌትነት እያስተማራችሁ እንድትሄዱ በማለት ጉዞውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የከተማ አስተዳደሩ ለተጓዦች ካዘጋጀው የስንቅ ድጋፍ በተጨማሪ የሁለት ሚሊየን ብር ስጦታም አበርክቶላቸዋል፡፡
125ኛውን የአድዋ ድልን በማስመልከት ከአዲስ አበባ እና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 125 የጉዞ አድዋ ተሳታፊዎች ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣የሃማኖት አባቶች ፣አባት አርበኞች ፣ከፍተኛ አመራሮች እና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በዛሬው ዕለት መሸኘታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.