Fana: At a Speed of Life!

የአድዋ ድል የህዝቦች የጋራ ውጤት በመሆኑ ለወቅታዊ የሀገሪቱ ችግሮች እንደ ምሳሌ ሊቀርብ ይገባል -ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአድዋ ድል የህዝቦች የጋራ ውጤት በመሆኑ ለወቅታዊ የሀገሪቱ ችግሮች እንደ ምሳሌ ሊቀርብ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ምሁራን እንደገለጹት፥ ድሉ በአንድነትና በህብረት የተመዘገበ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሊኮሩበት ይገባል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር አለምሰገድ በልዳዶስ፥የአድዋ ድል በአንድነት የመጣ በመሆኑ ተምሳሌትነቱ ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄ መሆን ይችላል ነው ያሉት።

በወቅቱ በሀገሪቱ ሁሉም አቅጣጫ የነበረው ህዝብ ለዳር ድንበሩ ተዋድቆ፤ አንድነት እና የህብረት ጥንካሬን በተግባር በማረጋገጥ ለዛሬው ትውልድ አርአያ መሆኑን አውስተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር ከተቦ አብድዮ በበኩላቸው፥ የአድዋ ድል የህዝቦች የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ድል እና የትብብር ውጤት መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህሩ አቶ ንጋቱ አበበም አሁን ኢትዮጵያ እየተጋፈጠችው ካለው ዋልታ ረገጥ አካሄድ ለመውጣት የጋራ ታሪካችን ገጾች ገልጦ ማስተዋል ይገባል ይላሉ።

በተጨማሪም ከመነጣጠል በጋር መስራት እና ህብረት የቀደምት አባቶቻችንን ጠንካራ ተሞክሮ በመሆኑ ልንማርበት እንደሚገባ አብራርተዋል።

ምሁራኑ የአድዋ ድል የአንድነት እና የትብብር ውጤት መሆኑን በመረዳት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚስተወሉ ችግሮች ለመፍታት ልንጠቀምበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሃይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.