Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሀገራትን የኢነርጂ ሀብት በማሰባሰብ ፤ ቀጠናዊ ትብብርን በማጠናከር አፍሪካን በሃይል ልማት ማስተሳሰር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራትን የኢነርጂ ሀብት ማሰባሰብ ፤ ቀጠናዊ ትብብርን ማጠናከርና ውህደትን ማጎልበት ያስፈልጋል ሲሉ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በአለም አቀፉ የሃይል ትስስር ልማትና ትብብር ድርጅት ውስጥ አፍሪካን ተሳታፊ ለማድረግ የተዋቀረውን ኮሚቴ ስራ ለማስጀመር በኦንላይን በተደረገ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

ሚኒስተሩ ዶክተር ኢነጂነር ስለሺ የአለም አቀፍ የኢነርጂ ትስስር ልማትና ትብብር ድርጅት የአፍሪካ ተወካይ ኮሚቴ ምስረታና በሃይል መስክ የትብብር ሴሚናር መካሄዱ በሃይል ቅርቦት ጉዳይ ባለድርሻ አካላትን፣ መሪዎችና ባለሙያዎችን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ለማካሄድ ከፍተኛ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የኃይል ኢንዱስትሪ ውስጥ በፕሮጀክት ልማት እና በአቅም ግንባታ ላይ ትብብርን በማጎልበት እና በማጠናከር ላይ ውይይቶችን በማመቻቸት የአፍሪካ ቀጠና ኮሚቴ መቋቋሙ የአፍሪካን የኃይል ትስስር ያሳድጋልም ነው ያሉት ፡፡

በዚህ ረገድ በአፍሪካም ሆነ ከዚያ ባሻገር የኃይል ትስስርን ለማበረታታት የደቡብ-ደቡብ የሃይል የትብብር ኔትወርክን ለማጎልበት የአፍሪካ ክልላዊ ኮሚቴን ማቋቋም ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካ ብዙ ተግዳሮቶች አሏት ያሉት ሚኒስሩ የዜጎችን የኑሮ ጥራት ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ትምህርት፣ ጤናን እና የንጹህ ውሃ አቅርቦ እጥረት በተጨማሪ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የነፍስ ወከፍ የኃይል ፍጆታ ዝቅተኛ መሆን በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ክፍሎች ለሚገኙ መንግስታት ከፍተኛ የቤት ሰራ ሆኖ ዘልቋል በማለት አንስተዋል ፡፡

በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማምጣት ዋናው እንቅፋት ነው ያሉ ሲሆን ለአብነትም ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አመታት ዜጎቿን በኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም ከ110 ሚሊየን የሀገሪቱ ዜጎች 55 በመቶ ያህሉ አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ገልፀዋል፡፡

ይህን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተግዳሮት ለመቅረፍ መንግስት በአውሮፓውያኑ 2025 በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ፍኖተ ካርታ በማውጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይል አቅም በአሁን ወቅት 4 ሺህ 413 ሜጋ ዋት የደረሰ ሲሆን በ2030 ለሀገር ውስጥም ሆነ ለወጭ ገበያ ሃይል ለማቅረብም የሃይል አቅምን 20 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ መታቀዱን መናገራቸውን ከውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.