Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ሀገራዊ እቅዶቿን በአጀንዳ 2063 ላይ ከተቀመጡ ግቦች ጋር በማስተሳሰር ለተግባራዊነታቸው እየሠራች ነው – የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሀገራዊ እቅዶቿን በአጀንዳ 2063 ላይ ከተቀመጡ ግቦች ጋር በማስተሳሰር ለተግባራዊነታቸው እየሠራች መሆኗን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በአፍሪካ የአጀንዳ 2063 የአስር ዓመታት አፈጻጸም እና ቀጣይ አስር ዓመታት እቅድ ላይ የሕብረቱ አባል ሀገራት የፕላንና ልማት ሚኒስትሮች በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ÷ ኢትዮጵያ ሀገራዊ እቅዶቿን በአጀንዳ 2063 ላይ ከተቀመጡ ግቦች ጋር በማስተሳሰር ለተግባራዊነታቸው እየሠራች መሆኗን አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ተግዳሮት ቢሆኑም÷ እነዚህን ችግሮች በመቋቋም የተገኘው ውጤት ለቀጣይ 10 ዓመታት ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር÷ ባለፉት ሦስት ዓመታት 18 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውንም ነው ዶክተር ፍጹም ያስረዱት፡፡

በተያዘው ዓመትም ከ6 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል በአራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ይህ ተግባርም የአፍሪካ ሕብረት በአጀንዳ 2063 ያስቀመጠውን ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚና ማህበረሰብን መገንባት በሚል የተቀመጠው ግብ በኢትዮጵያ በመልካም አፈጻጸም ላይ መሆኑን ማሳያ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በአቪየሽን ዘርፍ እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ያገኘቻቸውን ውጤቶች በማጎልበትና ተግዳሮቶችን በመፍታት ለአጀንዳ 2063 ስኬታማነት የበኩሏን እንደምትሠራም አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.