Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን 28 ሃገራት ማጽደቃቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጠናን በመጭው ሐምሌ ወር በይፋ ስራ ለማስጀመር 54 ሀገራት መፈረማቸውን

የህብረቱ ኮሚሽን የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አምባሳደር ሙቻንጋ አልበርት ገለጹ።

ነጻ የንግድ ቀጠናውን ለመመስረት የተደረሰውን ስምምነት 28 ሃገራት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ስምምነቱ እንዲጸድቅ አድርገዋል።

የፊታችን የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የኀብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ቀሪ የአፍሪካ ሃገራት ስምምነቱን እንዲያጸድቁ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ አምባሳደር ሙቻንጋ አልበርት ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ስምንት ጥቅል እና ሰባት ዝርዝር ዓላማዎች አሉት።

ከጥቅል ዓላማዎቹ ውስጥ በአፍሪካ የተቀናጀ ጥልቅ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ለመፍጠር የዕቃ፣ የአገልግሎትና የሰዎች ዝውውርን መፍጠር እንዲሁም በስምምነት ላይ የተመሰረተ የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ነጻ ገበያ መፍጠር ይጠቀሳሉ።

አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ የአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጠና በመጭው ሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም በይፋ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ በተካሄደው የኅብረቱ የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ የአህጉሪቱን ነጻ የንግድ ቀጠናን ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ስራ ለማስጀመር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውሰዋል።

የምርትና የስርጭት ሰነዶችን በአፍሪካ ሃገራት ለሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በሃገር አቀፍ ደረጃ እስከ መጭው ግንቦት ወር ድረስ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

እንዲሁም በመነሻ ህጎች ላይ ገዢ የሆነ አካልን ማቋቋም፣ በዕቃዎች ታሪፍ ላይ ስምምነት ማሳደጊያ መርሃ ግብር ማዘጋጀት፣ ከታሪፍ ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን የቁጥጥርና የሪፖርት መሰናክሎችን ማስወገድ ይገኙበታልም ነው ያሉት።

የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት፣ ክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦችና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በጋራ የሚሳተፉበት ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ባለፈው አመት መጋቢት 12 ቀን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቋን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.