Fana: At a Speed of Life!

የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ለኮቪድ 19 ወረርሺኝ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል – ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ ፣መስከረም 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ለኮቪድ- 19 ወረርሺኝ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በጥንቃቄ ማክበር እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

ሚኒስትሯ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኢሬቻ በዓል በመሰባሰብ የሚከበር ማኅበራዊ ግንኙነቶችንና ትስስሮች የሚጠናከሩበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ በዓለምና በሃገር አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ይህን በዓል በተለየ መልኩ ማክበር ይገባል ነው ያሉት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በወረርሺኙ የሚጠቁ፣ በጽኑ የሚታመሙና ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል።

በመሆኑም ኢሬቻ በሚከበርበት ወቅት እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት የቫይረሱን ተጋላጭነት መቀነስና በጥንቃቄ ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።

በአከባበሩ ወቅት እንደ ወትሮው በርካታ ሰዎች መሰባሰብ አይኖርባቸውም ያሉት ሚኒስትሯ ሁሉም በያሉበት ሆነው መርሃ ግብሩን በሚካሄደው የቀጥታ ስርጭት ቢከታተሉ መልካም ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅቱ የወረርሺኝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ኅብረተሰቡም የሚያደርገውን ጥንቃቄ ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚኒስትሯ ለመላው የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎችና ተሳታፊዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.