Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ይበልጥ ይጠናከራል -አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ሁሉን አቀፍ የሆነው የኢትዮጵያና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት ዲጂታል ኢኮኖሚን ጨምሮ በአዳዲስ የትብብር መስኮች ይበልጥ እንደሚጠናከር የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ገለጹ።
ሚኒስትሩ በሴኔጋል መዲና ዳካር ሕዳር 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄደውን ስምንተኛውን የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም (ፎካክ) አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፎካክ ማዕቀፍ በቻይናና አፍሪካ መካከል የመሰረተ ልማት ግንባታ ትስስር በመፍጠር የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ፣ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግና የስራ እድል ፈጠራን በማበረታታት ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ፕሮጀክት ከቀደምት የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ስኬቶች መካከል መሆኑን ጠቅሰው በአፍሪካ አገራት መካከል ትብብርን በመፍጠርና የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን በማገዝ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተናግረዋል።
ቻይና የኢትዮጵያ ትልቁ የንግድ አጋር እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምንጭና በመሰረተ ልማት ግንባታም ትልቅ ተሳትፎ እያደረገች ያለች አገር ናት” ያሉት ሚኒስትሩ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።
በቻይና-አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ባገኘችው ድጋፍ አማካኝነት የተገነቡ በርካታ መንገዶች የኢትዮጵያዊያን የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻልና የንግድ ስርዓቱ ላይ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከቻይና የሚገኙ ድጋፎች አየር መንገዶችን፣ የውሃ ፕሮጀክቶችን፣ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉም ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ግንባታ፣ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክትና በቻይና ድጋፍ ወደ ሕዋ የመጠቁት ሁለት ሳተላይቶች በኢትዮጵያና ቻይና መካከል በክህሎት ማበልጸግ ያለውን ትብብር ይበልጥ እንዳጎለበተው አመላክተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጋረጠውን ፈተና ጨምሮ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ኩነት ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ የሆነ ግንኙነታቸው ባለበት መቀጠሉንም ገልጸዋል።
አሁንም ሁሉን አቀፍ የሆነው የኢትዮጵያና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በዲጂታልና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በኤሮስፔስና በሌሎችም አዳዲስ የትብብር መስኮች ይበልጥ ይጠናከራል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በሴኔጋል መዲና ዳካር የሚካሄደው ስምንተኛው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም(ፎካክ) ስኬታማ እንዲሆን ምኞታቸውን መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1970 እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.