Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ጥሩ የትብብር ማሳያ ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ለአፍሪካ ቻይና ትብብር ጥሩ ማሳያ መሆኑን ተናገሩ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሺንዋ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኢትዮጵያ እና ቻይና ላለፉት 50 ዓመታት የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላቸው አንስተዋል።

በዚህም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለአፍሪካ ቻይና ትብብር ጥሩ ምሳሌ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከጀመሩበት የፈረንጆቹ 1970 ጀምሮ በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉት ትብብር እያደገ መምጣቱንና በብዙ መልኩ መለወጡንም ጠቅሰዋል።

በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የሃገራቱ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በደህንነት ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአካዳሚክ እና አቅም ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉንም አውስተዋል።

ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ወደ ሁለገብ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በፈረንጆቹ 2017 ከፍ ለማድረግ ከተስማሙ ወዲህ አጋርነታቸውን ማሳደግ ችለዋልም ነው ያሉት አምባሳደር ዲና።

ትኩረቱን በንግድና ልማት ባደረገውና በተመድ በሚዘጋጀው ኮንፈረንስ የወጣ ሪፖርት ቻይና በፈረንጆቹ 2019 በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗን ያመላክታል።

በዚህም ቻይና በኢትዮጵያ አዲስ ከፀደቁ የውጭ ፕሮጀክቶች ውስጥ 60 በመቶውን ትይዛለች ነው ያለው ።

አምባሳደር ዲና በቆይታቸው ሃገራቱ ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ትብብር በህክምናው ዘርፍ በተለይም ኮቪድ19ኝን በመከላከል ረገድ መሻሻል የታየበት ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ወረርሽኙ የሚያስከትለውን አደጋ ለማስወገድ ሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና ለማሻሻል እንደምትሰራም አስረድተዋል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.