Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ፡፡

የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ በሃገራቱ መከካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግም ባለድርሻ አካላት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የደቡብ አፍሪካ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ አጋጣሚዎችን እንዲጠቀሙ እና መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቢዝነስና ኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችሉ የተለያዩ ምክረ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ጆን ሮቻ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የገበያ፣ ኢንቨስትመንት እና ቢዝነስ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ሃገራቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ እንደ አፍሪካ ነጻ ገበያ ቀጠና አይነት በባለብዙ ወገን አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ መድረኮች ላይ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅና ለመጠቀም መስራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

በፎረሙ ላይ ከሃገራቱ የተውጣጡ በግብርና ማቀነባበር፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በኬሚካል፣ በጤና ዘርፍ ግብዓት ማምረቻ እና በኃይል ማመንጫ ዘርፎች የንግድና ኢንቨስትመንት ያሉ ምቹ ሁኔታዎች ላይ ውይይት መደረጉን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡

ፎረሙ በሃገራቱ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ እና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርን ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.