Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግስት በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ሱዳናዊያን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ሱዳናዊያን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ አደረገ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በጎርፍ ለተጎዱ ሱዳናዊያን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ ካርቱም ገብቷል።
የልኡካን ቡድኑ ካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ተጠባባቂ ሚኒስትር ኦማር ቀመር-አልዲን እስማኤል እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አካላት አቀባበል አድርገውለታል።
አቶ ገዱ በሰብአዊ እርዳታ ርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር ወንድምና እህት የሆነው የሱዳን ህዝብ ያጋጠመውን ችግር ኢትዮጵያዊያን እንደራሳቸው የሚያዩት መሆኑንና ይህንን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ስም ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሱዳናዊያንን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ከሱዳን ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን አቶ ገዱ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር መግለፀቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የልኡካን ቡድኑ በጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሱዳናዊያን አገልግሎት የሚውል የተለያየ መጠን ያለው የእለት ደራሽ አልሚ ምግብ፣ ዱቄት፣ መድሃኒት፣ ስኳር፣ የአልጋ አጎበር እና ሌሎች ልዩ ልዩ ቁሳ ቁሶችን በመያዝ ነው ወደ ካርቱም ያቀናው።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ረጅም ኪሎ ሜትሮችን የሚያቋርጥ ድንበር ከመጋራታቸውም በተጨማሪ የሁለቱ ሀገር ህዝቦች በደም፣ በሀይማኖት በባህልና በቋንቋ የተሳሰሩ ወንድምና እህት በመሆናቸው መሰል ደጋፎች የሁለቱን ሀገር ህዝቦች ይበልጥ ለማቀራረብ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.