Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ጥቂት ቀናት ያስመዘገበው ድል የሚደነቅ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕግ ማስከበር ተልዕኮው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ጥቂት ቀናት ያስመዘገበው ድል የሚደነቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ሠራዊቱ ትናንት ምሽት በአዲግራት ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ዛሬ ደግሞ አዲግራትን ከሕወሓት ኃይል ሙሉ በሙሉ ነፃ አውጥቷል ብለዋል።

የፌደራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው ከተማዎችና አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች፣ በጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸው ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መመለስ ጀምረዋልም ነው ያሉት።

ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን፣ ሰብአዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች የሚሟሉበትን መንገድ እንደሚመቻቸም አስታውቀዋል፡፡

የሰብአዊ ድጋፍ ክንውኖችን ለመከታተል በፌደራል መንግሥት የተዋቀረው ከፍተኛ ኮሚቴ፣ ተመጣጣኝ እና ወቅታዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚያስችል መረጃን እንዲያሰባስቡ ተጨባጭ ሁኔታውን የሚያጣሩ ልዑካንን ወደ ስፍራው መላኩንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ይህ ኮሚቴ ባለፉት ቀናት መኖሪያቸውን ጥለው የተሰደዱት ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መሥራቱን ይቀጥላልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ አጠቃላይ ደኅንነት እና ጤንነት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ ስለሆነ፣ በትግራይ ክልል መረጋጋት እንዲሰፍን እና ዜጎች ከጉዳት እና እጦት ነፃ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.