Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኦፓል፣ ኤመራልድና ሳፋየር ማዕድናትን ሊያገበያይ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኦፓል፣ ኤመራልድና ሳፋየር ማዕድናትን ሊያገበያይ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማዕድን ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስገባት ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ይታወሳል።

በዚህም የማዕድን ምርቶችን ለማገበያየት በሁለቱ ተቋማት በተዘጋጀው የምርት ኮንትራት ላይ ከአቅራቢዎች፤ አምራቾችና የክልሎች ተወካዮች ጋር ምክክር ተካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ፥ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራ በማከናወን የኮንትራት ዝግጅትና የግብይት ሞዳሊቲ ተዘጋጅቷል።

ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በተሻለ መልኩ እንድታገኝ ለማስቻል የማዕድን ዘርፉ ያሉበትን ባህላዊና ኋላቀር የግብይት ስርዓት በማስወገድ ዘመናዊ፣ ግልፅና ተጠያቂነት የተላበሰ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሴክተሩ ዘመናዊ፣ ግልፅና ተገማች የግብይት ስርዓት በመፍጠር አምራቹ ብሎም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል ለመፍጠር ማእድናቱ ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ መቀላቀላቸው የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ነው የጠቆሙት።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ውይይትና ተሳትፎ በማድረግ የማዕድን ግብይት ኮንትራቱን በተሻለ ለማዳበር የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ወንድምአገኘሁ አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የማዕድን ዘርፍ በርካታ ዕድሎችና አቅሞች ያሉት በመሆኑ የግብይት ስርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ መታሰቡ ተገቢ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ሆኖም በዘርፉ ከጥራት አወሳሰንና አመዳደብ ጋር የሚታዩ ነገሮችን ከወዲሁ ማጤን እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአቅራቢውንና አምራቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አሁንም ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና የግብይት ስርዓቱ የበለጠ በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ከታች ካሉ አምራቾች ጋር ሰፊና በቂ ምክክር ሊደረግ እንደሚገባም መጠቆማቸውን ከምርት ገበያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.