Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበት ቅርንጫፍ ከፈተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴት ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁለተኛውን ቅርንጫፍ ልደታ አካባቢ ከፈተ።

በቅርንጫፉ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና አቶ ባጫ ጊና፥ ባንኩ ከ77 ዓመታት በላይ በዘለቀው የአገልግሎት ዘመኑ በመላ ሀገሪቱ ከከፈታቸው ከ1 ሺህ 560 በላይ ቅርንጫፎች ውስጥ በሴቶች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ በእለቱ የተመረቀው ልደታ ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛው ነው።

ባንኩ ባለፈው አመት ቦሌ አትላስ አካካቢ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሠጥ ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን መግለፃቸውንም የባንኩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሣደግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ ባጫ፣ ከነዚህም ውስጥ የሴቶችን የፋይናንስና ኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት የቁጠባ ሒሳብ ተጠቃሚዎች ከመደበኛው የቁጠባ ሒሳብ በተሻለ ወለድ የሚያገኙበት አሰራር በማመቻቸት የቀረበው የሴቶች የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት አንዱ መሆኑንም ነው የገለፁት።

የሴቶች የቁጠባ ሂሳብ አገልግሎት ላይ ከዋለ በኃላ ከ47 ቢሊየን ብር በላይ በቁጠባ ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን፥ ይህን አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞችን ቁጥርም ከ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ማድረስ መቻሉንም አክለው ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ባንኩ የሴቶችን የስራ ፈጠራ አቅም ሊያሳድግ የሚችል የብድር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ራሱን የቻለ ክፍል በመቋቋም ሂደት ላይ መሆኑንም አቶ ባጫ ጠቁመዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.