Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር ሀይል ያሰለጠናቸውን አብራሪዎች አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘’ነብሮች 2014’’ በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ አየር ሀይል በበረራ ሙያ ያሰለጠናቸውን አብራሪዎች አስመረቀ።
በምረቃ መርሐ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ተመራቂዎቹ በመጀመሪያ ደረጃ በረራ ማሰልጠኛ አውሮፕላን፣ በትራንስፖርት ሄሊኮፕተር፣ በተዋጊ ሄሊኮፕተር፣ በቪ አይ ፒ ሄሊኮፕተር እና በትራንስፖርት አውሮፕላን ለተከታታይ አመታት የሰለጠኑ መሆናቸው ተገልጿል።
ለተመራቂዎቹም ዲፕሎማና የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።
ይህም አየር ሀይሉ የኢትዮጵያን አየር ክልል የመጠበቅ ትልቅ ቁመና ላይ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ተነስቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚህ ወቅት፥ ከልጅነት እስከ እውቀት ኩራት የሚሰማኝ የአገሩን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ውድ ሕይወት ለሚከፍለው አገር አገር የሚሸት የአገር መከላከያ ሰራዊቱ መካከል ስገኝ ነው ብለዋል።
አየር ኃይሉ ባለፉት 90 ዓመታት አኩሪ ገድል ፈፅሟል፤ ለአገር ሉዓላዊነት መስዕዋትነት ከፍሏል ሲሉ አንስተው ፥ አየር ኃይሉ በየጊዜው የሚመጥን አቅም መያዝ እንዳለበት ገልጸዋል።
የተቋማት ሪፎርም ውጤቱንም በአየር ሀይሉ ትርዒቶች መመልከታቸውንም ጠቅሰዋል።
ለአየር ኃይሉ የተራቀቀ ትጥቅና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሟላት አስፈላጊ መሆኑንና ለዚህም በቂና ብቁ የሰው ኃይል መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልፀው ፥ ከአብራሪዎቹ በተጨማሪም በአጠቃላይ የአየር ሀይል ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ማብቃት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የአየር ኃይሉን መምሪያ የፈጠረው ምቹ አካባቢ ስራ አስገራሚ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ ፥ ይህም ምርታማ የሰው ኃይል ለማፍራት ያግዛል ፤ የመከላከያ እና የደህንነት ተቋማት ሪፎርም ማጠናከርና ለተልዕኮ ብቁ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ መንግስታዊ ስርዓት ቢለወጥ የማይለዋወጥ አገር የሚጠብቅ በመሆኑ እኛም አገርን ለትውልድ ማሻገር አለብን ብለዋል።
ፕሬዚዳንቷ አክለውም ፥ የሰው ልጅ በሕይወት የመኖር መብት መጠበቅ እንደሚገባና ሁላችንም ከቃል ባለፈ አገርን በተግባር መጠበቅ አለብንም ነው ያሉት።
ለታላቋ አገር ታላቅ አየር ኃይል መገንባት ያስፈልገናል ሲሉም ገልጸዋል ፕሬዚዳንቷ።
ኢትዮጵያን የሚመጥን እንደከዚህ ቀደሙ በአፍሪካ የሚፈራ እና የሚከበር አየር ሀይል ለመገንባት እየተሰራን መሆኑን የገለጹት ደግሞ÷ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አየር ሀይል እስከ ደርግ ጊዜ በአፍሪካ የተከበረና የሚፈራ እንደነበር አስታውሰው፥ እስከ ለውጡ ድረስ የማፍረስ ስራ ተሰርቶበት ደካማ ተደርጓል ብለዋል።
አየር ሀይሉ በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ታግዞ ወደ ቀደመው ቁመና እየተመለሰ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የአየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው÷ ሰራዊት ሀገር እንጂ ብሔር የለውም በሚል መሪ ቃል የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረግ ሰራዊቱ ከብሔርተኝነት፣ ከፖለቲካና ከሀይማኖት ጽንፈኝነት አመለካከት ነጻ የሆነ ሰራዊት ለመገንባት ተችሏል ብለዋል።
ዛሬ የተመረቁ አብራሪዎችም የዚህ ፍሬ መሆናቸውን ገለጹት ዋና አዛዡ÷ የአቪዬሺን ቴክኖሎጂ ከደረሰበት አንጻር ገና ይቀረናል ብለዋል።
የውጊያ መሰረተ ልማት ማሻሻል ቀዳሚ ግብ ሆኖ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለታላቅ ሀገር የሚመጥን አየር ሀይልም ይገነባል ነው ያሉት።
በታሪኩ ለገሰ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.