Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመረው ሂደት መቆሙን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመረው ሂደት መቆሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የ2013 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በገቢ ደረጃ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 80 ነጥብ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሲሰበሰብ፤ 97 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

ይህም በወጪ ደረጃ የበጀት እጥረት እንደነበር ጠቅሰው፥ እጥረቱን ለመሸፈን ከብሄራዊ ባንክ ወጪ በማድረግ የዋጋ ግሽበት እንዳይጨምር በግምጃ ቤት ሰነድ አማካኝነት ከግል ባንኮች በመደበር እንዲሸፈን ተደርጓልም ነው ያሉት።

በብድር እና እርዳታ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 474 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በሚደረግ ድጋፍ 131 ሚሊየን ዶላር ከጀርመን እና ከጃፓን መንግስት መገኘቱንም አስታውቀዋል።

ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።

ከፕራይቬታይዜሽን ጋር በተያያዘ በቴሌኮም ዘርፍ ከዚህ ቀደም ፍቃድ ይሰጣል ከተባለው ሁለት የቴሌኮም ኩባንያዎች በተጨማሪ ከመንግስት ጋር በጋራ የሚሰራ ለአንድ ተጨማሪ የቴሌኮም ኩባንያም ፍቃድ እንደሚሰጥም አውስተዋል።

ይህም በአጠቃላይ በያዝነው ዓመት ፍቃድ ይሰጣቸዋል የተባሉትን የቴሌኮም ኩባንያዎች ቁጥር ወደ 3 ከፍ እንደሚያደርገው እና ይህንን ለማስኬድም የፕራይቬታይዜሽን ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

የፕራይቬታይዜሽን አካል የሆነውን የሎጂስቲክስ ዘርፍ ግን ኢትዮጵያ የባህር ወደብ የሌላት በመሆኑ የሎጂስቲክ አገልግሎት እንዲሳለጥ ከማድረግ አንፃር ለግል ድርጅቶች ይሰጣል ነው ያሉት።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመረው ሂደት መቋረጡንም ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ስም እና ዝና እንዲሁም ትርፋማ ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ በመሆኑም መንግስት ይህን በመገንዘብ ፕራይቬታይዝ የማድረጉን ሂደት ማቋረጡን አስረድተዋል።

ከስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ፕሮጀክቶቹን ወደ ግል ለማዛወር የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑንም ነው በመግለጫቸው ያነሱት።

ለመንግስት የስራ ሀላፊዎች ሲ ኤም ሲ አካባቢ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን በጨረታ በመሸጥ እስከ 1 ቢሊየን ብር ለማግኘት መታቀዱንም ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።

ይህም ህንፃዎች በተገነቡበት አካባቢ የሪል ስቴት መንደር በመሆኑ እና ከደህንነት አንፃርም ጥያቄ የሚያስነሳ ስለሆነ ቤቶቹን ለመሸጥ ጨረታ ወጥቷል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ የሚገኙ የካቢኔ አባላት ህጋዊ ባልሆነ ምርጫ ተመርጠናል በሚል የሀገሪቱን ህገ መንግስት በመጣሳቸው አሁን ባለው ሁኔታ የገንዘብ ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል መንግስት በጀት እንደማይለቅም ነው የተናገሩት።

በትግራይ ክልል ለሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች በኩል በተጠና ሁኔታ እንዲደርሳቸው ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ከአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን ያክል ነው የሚለው ወደ ፊት የሚጠና ሆኖ፤ አሁን ላይ ከዓለም ባንክ በተገኘ 60 ሚሊየን ዶላር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ወረርሽኑ በኢትዮጵያ አቅም ብቻ የሚጠፋ ባለመሆኑ ከኢዳግ እና ከምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መከላከል ባለስልጣን ጋር በቅንጅት ለመስራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በፀጋዬ ንጉስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.