Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚበርባቸው የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹ የበረራ ቁጥር ጨመረ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለሟሟላት በሚበርባቸው የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹ የበረራ ቁጥር መጨመሩን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እያደገ የመጣውን የደንበኞች የጉዞ ፍላጎት ለሟሟላት በሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹ በሚሰጠው ሳምንታዊ መደበኛ የበረራ አገልግሎት ላይማሻሻያ ማድረጉን ነው ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የአገልግሎት ማሻሻውን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “እያደገ ለመጣው የደንበኞቻችን የጉዞ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት አሁን በምንበርባቸው የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቻችን የነበረውን መደበኛ ሳምንታዊ የበረራ አገልግሎት በመጨመራችን ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል˝ ብለዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚ “እስካሁን ስናደርገው እንደቆየነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የመከላከያ እርምጃዎችን በጥብቅ ዲሲፕሊን በአየር ማረፊያም ሆነ በበረራ ወቅት ተግባር ላይ በማዋል የኮሮና ቫይረስን ስርጭት እየተከላከልን የደንበኞቻችንን እና የሰራተኞቻችንን ደህንነት በመጠበቅ አገልግሎታችንን አጠናክረን እንቀጥላለንም˝ ነው ያሉት።

አየር መንገዱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን በመከላከል የመንገደኞቹንና የሰራተኞቹን ጤንነት ለመጠበቅ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች ደንበኞች ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በመሆኑም መንገደኞች በአየር መንገዱ ይፋዊ ድረ ገጽ፣ ቻት ቦት፣ ኢሜይል፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ እንዲሁም በአየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የጥሪ ማእከልና የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አማካኝነት የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

በእነዚህ የዲጂታል አማራጮች የሚቀርቡ አገልግሎቶች ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አብረው የሚሄዱ ከመሆናቸው ባሻገር፣ የደንበኞችን ፍላጎት ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

ደንበኞች በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ የበረራ ትኬታቸውን ተመዝግበው ሲገዙም የ10 በመቶ የትኬት ቅናሽ እንደሚያገኙ መግለጫው አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.