Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሁሉም የሙስሊም ማህበረሰብ ቤት ውስጥ የመስገድ ግዴታ ኃይማኖታዊ ብያኔ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሁሉም የሙስሊም ማህበረሰብ ቤቱ ውስጥ የመስገድ ግድታ ኃይማኖታዊ ብያኔን በዛሬው እለት ሰጠ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው፥ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ለመግታት ከዚህ ቀደም ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በተጨማሪ ሌላ ኃይማኖታዊ ብያኔ (ፈትዋ) መስጠቱን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት፦

1. በበሽታው የተያዙ እና በዕድሜ የገፉት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት እቤታቸው ውስጥ መስገድ ግዴታ ነው፤

2. የጤና ተቋማት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች የሚያወጧቸውን መመሪያዎች እና የሚሰጧቸውን ጥንቃቄና መከላከያ አቅጣጫዎች መቀበልና ስራ ላይ ማዋል ኃይማኖታዊ ግዴታ ነው ፤

3. በሽታው (ወረርሽኙ) ዛሬ ከተደረሰበት ደረጃ እና ስርጭቱ መንገድ ፍጥነት ከአስቸጋሪነቱ እና ከጉዳቱ አንፃር የጁምአና የጀመአ ሰላትን ለማስቆም የሚያስገድድ ሸሪአዊ ምክንያት በመሆኑ ፈትዋ ከተሰጠበት ከዛሬ መጋቢት 22 ጀምሮ በሽታው በሰው ልጅ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መቆሙ በጤና ባለሙያዎች እስከሚረጋገጥ ጊዜ ድረስ የጁምዓ ሰላትና የጀምአ ሰላት ታግዶ እንዲቆም የዑለማ ምክር ቤት ወስኗል።

4. በአምስቱም ወቅት ሶላት ሙኢዝኖች አዛን ያደርጋሉ፤ በአብዛኛው ሰው ወደ መስጂድ እንዲሄድ ሳይህን በየቤቱ እንዲሰግድ በማለት መናገር እንዳለባቸውም ተወስኗል።

5. በገጠርም ሆነ በከተማ በስብሰባ መልክ ኃይማኖታዊ ትምህርት መስጠት የበሽታውን ስርጭት ስለሚያባብስና ለህመምና ለሞት ምክንያት ስለሚሆን በሽታውን አላህ እስከሚያነሳው ድረስ የመማር ማስተማር ስራው እንዲቋረጥና እንዶቆም የዑለማ ምክር ቤት ወስኗል።

6. በህክምና ረገድ በሽታው የሚሰራጨው በእጅ ንክኪ ስለተረጋገጠ የበሽታውን ስርጭት ዛሬ በደረሰበት ደረጃ በእጅ በመጨባበጥ ሰላምታ መለዋወጥ የተከለከለ መሆኑንም ምክር ቤቱ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው፥ “በመስጂድ የሚከናወን ማናቸውም የጁመአ እና የጀመአ ሶላት የቂራትም፣ የዘኪር ስብሰባ እንዲቆም የተወሰነበት ሸሪዓዊ መሰረት ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሶሃቦች የተሰሙት ሐዲሶችና ነፍንስ ወይም ህይወትን የመጠበቅ ከሸሪዓዊ ተልእኮዎች አንዱና ዋንኛው ምክንያት በመሆኑ ነው” ሲልም ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.