Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት (ካውንስል) በዛሬው ዕለት በይፋ ተመስርቷል።

ምስረታው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች እና የተለያዩ ማህበራት ተወካዮች በተገኙበት ነው የተከናወነው።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ምክር ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች የሀገሪቱን ፍላጎትና ገበያ ማእከል ያደረጉ እንዲሆኑ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ጥራትና አግባብነትን ለማስጠበቅ እንዲቻል የሚኖረው ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የሀገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች በዓለም አቀፍ  ደረጃ እንዲመዘኑ እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያግዛልም ነው ያሉት፡፡

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ በመሆን በሚያደደርገው ጥናት መሠረት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ላይ ከምደባ ወደ ቅበላ የሚሸጋገሩበትን ሂደት እንደሚጀምሩም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው የምክር ቤቱ በይፋ መመስረት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን የሚመስል የትምህርት ሥርዓት ለመገንባት እየተሰራ ያለውን ሥራም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚደግፈውም ጭምር ፕሮፌሰር ሂሩት አንስተዋል።

ምክር ቤቱ የሁሉም የሙያ መስኮች ማህበራት ውክልና ያለውና የኢንዱስትሪ ማህበራትንና ተቀራራቢ ሲቪክ ማህበራትን አካቶ የተደራጀ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነፃነት ሲያገኙ፤ ተጠያቂነታቸው ለጥራት መለኪያ እንዲሆን ነፃና ገለልተኛ አካል ሆነው በትምህርት አግባብነት ማረጋገጥ ሥራ ሂደት ሙያ ነክ ተግባራትን በማገዝ በንቃት እንደሚሳተፉም ይጠበቃል ተብሏል።

በአዲሱ ሙሉነህ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.