Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና የንግድ ፎረም በሲሪላንካ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ፎረም በሲሪላንካ ኮሎምቦ ከተማ ተካሄደ።

ህንድ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲና በኮሎምቦ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ ፅህፈት ቤት በጋራ ትብብር ነው ፎረሙ ባለፈው ሳምንት በፈረንጆቹ የካቲት 6 ቀን 2020 የተካሄደው።

በፎረሙ በሲሪላንካ የሚገኙ ከ45 የሚበልጡ ባለሀብቶች፣ የተለያዩ ኩባንያ ባለቤቶችና የስራ ኃላፊዎች፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

እንዲሁም በሲሪላንካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሱሚዝ ዳሳና ያኬ ተገኝተዋል።

በህንድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታ በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ሲሪላንካ በፈረንጆቹ 1972 ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረታቸውን አስታውሰው፥ ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተቀራርበው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የኢኮኖሚ ግንኙነትን በሚመለከትም የተወሰኑ የሲሪላንካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንደተሰማሩ ገልጸው፥ የመንግስት የትኩረት መስኮች በሆኑት በግብርና ውጤቶች ማቀነባበር፣ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎችን በማምረት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን፣ በሃይል እና በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፎች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።

አምባሳደር ዶ/ር ትዝታ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማጠናከር መንግስት የተለያዩ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው፥ በዚህም የሲሪላንካ ባለሃብቶችና የንግድ ኩባንያዎች በሀገራችን ገብተው በተለያዩ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ለማገዝ ኤምባሲው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደረግ አረጋግጠዋል።

የቀድሞው በኢትዮጵያ የሲሪላንካ አምባሳደርና በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አምባሳደር ሱሚዝ ዳሳና ያኬ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት እየወሰዳቸው ያሉትን ዘርፈ-ብዙ  የሪፎርም ስራዎችን በቅርበት እንደሚከታተሉና እንደሚያደንቁ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የብዙ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን አውስተው፥ የሲሪላንካ ኩባንያዎችም ይህን መልካም እድል እንዲጠቀሙበትና በተለያዩ ዘርፎች ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።

በህንድ የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ከህንድ በተጨማ ሪታይላንድ፣ ሲሪላንካ፣ ኔፓል፣ ባንግላዲሽ፣ ቡታንና ካዛኪስታንን የሚሸፍን ሲሆን፥ በነዚህ ሀገራት የሚገኙ የተለያዩ ኩባንያ ባለቤቶች እና በንግድና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦችን ወደ ሀገራችን ለማስገባት በአሁኑ ወቅት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.