Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ጣሊያን የቢዝነስ ፎረም ተጠናቀቀ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትኩረቱን በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቱሪዝም ላይ ያደረገው የኢትዮ-ጣሊያን የቢዝነስ ፎረም መጠናቀቁን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ፡፡

በኤምባሲው አዘጋጅነትና በኮፊ ኢንዱስትሪያል አፍሪካና ሜዲትራኒያን እንዲሁም በቦንለይ ኤረዲ የህግ አማካሪ ድርጅት ተባባሪነት የተዘጋጀው የቢዝነስ ፎረሙ ለሁለት ቀናት በሮም ተካሄዷል።

በመድረኩ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በፖለቲካ፣ በኢኮሚኖና በማህበራዊ ዘርፍ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ ጠቅሰው÷ ግንኙነቱ በኢኮኖሚው መስክ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበው ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚመጡ ካምፓኒዎችም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

በሮም የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ በበኩላቸው÷በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ቱሪዝም ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅምና ሃብት እንዲሁም የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ባለሃብቶች በንግድና ኢንቨስትምንት ብሎም በቱሪዝም መስክ ተቀራርበው እንዲሰሩ በተለይ በዚህ በፎረም ተሳታፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ጣሊያናውያን ባለሃብቶች በየዘርፎቻቸው በሽርክና ለመስራት እድሉን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያና ጣሊያን ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹት በጣሊያን ውጭ ጉዳይ እና ልማት ትብብር ሚንስቴር ከሳህራ በታች የአፍሪካ ዳይሬክተር አምባሳደር ጉሴፔ ሚስትሬታ÷ኢትዮጵያ ሄደው ኢንቨስት ለሚያደርጉ ጣሊያናውያን ባለሃብቶች በእነሱ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ መግለፃቸውን ከሮም ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.