Fana: At a Speed of Life!

የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይፋ ሆነ።

በአገልግሎቱ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች የተለያዩ ተቋማት መሪዎች እና የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገልግሎቱ ከሃገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንዱ የሆነው ንግድን ማሳለጥ አንድ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

አገልግሎቱ ተግባራዊ ቢደረግም አሁንም ብዙ እንደሚቀር በመረዳትም የንግድ ዘርፉን ለማሳለጥ መስራት ይገባልም ነው ያሉት።

ለግሉ ሴክተር የተመቻቸ ነገር ተፈጥሮ አዳዲስ ነገር ማመንጨት ካልተቻለ ብልጽግናን ማረጋገጥ ስለማይቻል መንግስት ለዚህ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግልም አንስተዋል።

አዲሱ አገልግሎት አሰራሮችን በቴክኖሎጅ የተደገፈ በማድረግ ሌብነትን ለመቀነስ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አዲሱ የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ በሰጡት ማብራሪያም፥ ረቂቁ ሲጋራ እና መጠጥ ላይ ተጨማሪ ታክስ በመጣል የሚገኘው ገቢ በቀጥታ ወደ ጤና ሚኒስቴር ፈሰስ ይደረጋል ብለዋል።

ይህም አሁን ላይ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት ለመከላከል ይውላልም ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም አሮጌ መኪና በቅናሽ ዋጋ በማምጣት በትራፊክ አደጋ፣ ለመለዋወጫ ወጪ እና በነዳጅ ዋጋ ስንከፍል ቆይተናልም ብለዋል በማብራሪያቸው።

በረቂቁ መሰረት አዳዲስ መኪና ላይ የተጣለውን የታክስ ጫና መንግስት መቀነሱን ገልጸዋል።

አሮጌ መኪና፣ ሲጋራ እና የአልኮል መጠጦች ላይ የሚጣለው ተጨማሪ ኤክሳይስ ታክስ የማይቀር ሃሳብ በመሆኑ ወደ አዲሱ መንገድ መግባት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው አዲሱ ረቂቅ ገቢን ለማሳደግ ሳይሆን ብዙ ህይዎትን ለማዳን የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎትን ሃገራት ለንግድ ተወዳዳሪነት እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ንግድን ለማሳለጥና ቀልጣፋ አግልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፥ ረጅም ቀናት ይወስድ የነበረውን አሰራር ለማሻሻል እንደሚረዳም አውስተዋል።

በዓላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.