Fana: At a Speed of Life!

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በዙሪያው ባሉ ትምህርት ቤቶች በኮሮና ቫይረስ መከላከል ዙሪያ ስልጠና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በዙሪያው ባሉ ትምህርት ቤቶች መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች በኮሮና ቫይረስ መከላከል ዙሪያ ከነገ ጀምሮ ስልጠና ሊሰጥ ነው፡፡
 
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ስልጠናው ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መስፈርት በተገቢው ሁኔታ ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ የበኩሉን ሚና ለመወጣት በማሰብ የሚሰጥ ነው፡፡
 
ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች ዳግም እንዲከፈቱ ለመምህራን፣ የአስተዳደር እና ፅዳት ሰራተኞች ስልጠና መሰጠት እንዳለበት አስቀምጧል፡፡
 
ዶክተር ያሬድ ከአሁን በፊት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ የጤና ባለሙያዎች ፊት ለፊት ሆነው ሲያገልግሉ መቆየታቸውን አስታውሰው የትምህርት ቤቶችን ዳግም መከፈት ተከትሎ ደግሞ አስተማሪዎች የተቀመጠውን የቫይረስ መከላከያና መመሪያ እንዲከተሉ የማድረግ እና የማስተማር ሃላፊነት እንደተጣለባቸው አንስተዋል፡፡
 
ሆስፒታሉም ስራው ውጤታማ እንዲሆን በማሰብ ስልጠና ለመስጠት ማሰቡን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም ሆስፒታሉ በኮሮና ቫይረስ ህሙማን ማቆያ እና ማገገሚያ ማዕከልነት የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰው፥ ሌሎች የጤና ተቋማት በአካባቢያቸው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተመሳሳይ ስልጠና ይሰጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
 
ስልጠናው መምህራን ተገቢውን መስፈርትና መመሪያ በማክበር የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች እንዲተገብሩና በስነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አውስተዋል፡፡
 
 
በስላባት ማናዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.