Fana: At a Speed of Life!

የእርግብ አተር፣ ቀይ ዥንጉርጉር ቦሎቄ እና ፒንቶ ቢን የተባሉት ምርቶች ግብይታቸው በምርት ገበያ እንዲሆን ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእርግብ አተር፣ ቀይ ዥንጉርጉር ቦሎቄ እና ፒንቶ ቢን የተባሉት የግብርና ምርቶች ግብይታቸው በኢትዮጵ ምርት ገበያ ብቻ እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡

በ2012 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ለማግኘት የታቀደው ገቢ ሙሉ በሙሉ ላለመገኘቱ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች እንዱ የወጪ ንግድ ምርቶች አቅርቦት እጥረት መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በ2013 በጀት ዓመት የአቅርቦት መጠኑን በማሻሻል ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ ከዚህ በፊት ግብይታቸው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሚፈጸሙ የወጪ ንግድ ምርች በተጨማሪ ሦስቱ የግብርና ምርቶች ግብይታቸው በኢትዮጵ ምርት ገበያ ብቻ እንዲፈጸም መወሰኑን ነው ያስታወቀው።

የእርግብ አተር፣ ቀይ ዥንጉርጉር ቦሎቄ እና ፒንቶ ቢን በህገ-ወጥ እና በኮንትሮባንድ እየባከኑ የነበሩ ምርቶች መሆናቸውም ነው የተገለፀው።

በሚኒስቴሩ የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚህም የተነሳ በ2011/12 ምርት ዘመን የተመረተና በበልግ የተመረተ ምርት በክምችት ያላቸው አቅራቢዎች፣ ጅምላ ነጋዴዎች እና ላኪዎች የ2012/13 ምርት ዘመን አዲስ ምርት ከመድረሱ በፊት እስከ መስከረም 30/2013 ዓ.ም ድረስ አቅራቢዎችና ጅምላ ነጋዴዎች ለላኪዎች ሸጠው ላኪዎች ደግሞ ወደ ውጪ ልከው እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤው የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የመጀመሪያ የግብይት ማዕከላት እንዲያዘጋጁ፣ህጋዊ አቅራቢዎች አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት ዝግጁ እንዲሆኑና ህገ-ወጥ የምርት ግብይትና ዝውውርን ለመቆጣጠር አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት እንዲያደርጉ ነው ያሳሰቡት።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርቶቹን የኮንትራት ሰነድ፣ የምርት መቀበያ ማዕከላትና የገበያ መሰረተ-ልማቶች ከወዲሁ ዝግጅታቸው እንዲጠናቀቅም ተጠይቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.