Fana: At a Speed of Life!

የእስራኤል ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት ሱዳንን ሊጎበኙ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት ሱዳንን ሊጎበኙ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ይህ የተሰማው አንድ የንግድ አውሮፕላን ከቴልአቪቭ ተነስቶ ካርቱም ማረፉ ከተነገረ በኋላ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ ሳምንት ይካሄዳል በተባለው ጉብኝት ልዑኩን ማን እንሚመራና መቼ እንደሚነሱ አለመታወቁን ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል አርሚይ ሬድዮን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ከቀናት በፊት ሱዳን ከአሜሪካ ሽብርተኝነት መዝገብ ለመውጣት ከዓመታት በፊት በኬንያና በታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶች 335 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል መስማማቷን ገልጻለች፡፡

ይህን ተከትሎም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ሱዳንን ከሽብርተኝነት መዝገብ ለመሰረዝ አሜሪካ ሂደት መጀመሯን ተናግረዋል፡፡

ፖምፔዮ ሂደቱን ተከትሎ ሱዳን ከእስራኤል ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምትጀምር ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት መካከል ከሳምንታት በፊት የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችና ባህሬን ከእስራኤል ጋር ወደ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ይህንንም ተከትሎ በዚህ ሳምንት የመጀመሪያው የንግድ አውሮፕላን ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በመነሳት ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤል አርፏል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.