Fana: At a Speed of Life!

የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ጤናና የስርዓተ ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል ያለመ የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእናቶችና ጨቅላ ህፃናትን ጤናና የስርዓተ ምግብ ሁኔታን ይበልጥ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ፡፡
“የተጠናከረ የጋራ ጥረት ለተመጣጣኝ የጤና ልማት” በሚል ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት ÷ በሀገሪቱ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለማሻሻል እንዲሁም የመላውን ህብረተሰብ የጤና አገልግሎትና ተደራሽነት ለማስፋት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ፡፡
በክልሉ በሰለጠነ ባለሙያ የወለዱ እናቶች ሽፋን 40 በመቶ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፥ የህጻናት ክትባት መሻሻል ቢታይበትም አሁንም ዝቅተኛ ሽፋን እንዳለው አንስተዋል፡፡
የህጻናት መቀንጨርን ከመቀነስ ጋር በተያያዘ በክልሉ አበረታች ውጤት መመዝገቡን በመጥቀስ ችግሩ አሁንም የተቀናጀ ጥረትን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡
የሀይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው ÷ መንግስት ባለፉት 20 ዓመታት የእናቶችንና ህፃናትን ጤና፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ የሥርዓተ-ምግብ ሁኔታን ለማሻሻል ፖሊሲ ቀርፆ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ስራዎች ካስገኟቸው ውጤቶች መካከልም ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ሞትና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የሚከሰት የእናቶች ሞት መቀነስ ተጠቃሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ደግሞ በክልሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ ስርጭትን በመከላከሉ ረገድ የተለያዩ ስራዎች በሰፊው ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ስርጭቱ በሀገር አቀፍ ካለው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ የባለድርሻ አካላትን የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ መናገራቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.