Fana: At a Speed of Life!

የእንቦጭ አረምን ማስወገድ ያስችላል የተባለው ቴክኖሎጂ ወደ ስራ መግባቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጣና ሃይቅ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ማስወገድ ያስችላል የተባለው ቴክኖሎጂ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል።

የጣና ሃይቅ እና የሌሎች ውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወልዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በሃይቁ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ካለፈው ህዳር ወር እስከ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም በተደረገ ንቅናቄም 1 ሺህ ሄክታር የእንቦጭ አረም ማስወገድ መቻሉን ነው የገለጹት።

አረሙን በቀላሉ ማስወገድ የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ስራ የማስገባት እንቅስቃሴ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት አሁን ላይ በተለያዩ ባለሙያዎች እና ድርጅቶች ከቀረቡት የፈጠራ ውጤቶች ውስጥ የተሻለ እና ውጤታማ የሆነውን በመምረጥ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል።

ወደ ስራ የገባው ቴክኖሎጂም በፎርክ ወይም በሬክ አማካኝነት በትራክተር የሚጎተት ማሽን መሆኑን ዶክተር አያሌው አስረድተዋል።

ማሽኑ በአንድ ጊዜ ከ48 እስከ 50 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የእንቦጭ አረምን ማስወገድ የሚያስችል ሲሆን፥ የሃይቁ ጥልቀት በጨመረ ቁጥር ለስራ የበለጠ እንደሚቀልም ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅትም ሁለት ማሽኖች ከአማራ ብድርና ተቋም በተገኙ ሁለት ትራክቶች በመታገዝ ስራ ላይ መሆናቸው ነው የተገለፀው።

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ማሽኑን መጎተት የሚያስችሉ ተጨማሪ 10 ትራክቶች መስጠቱን ተከትሎም በቀጣይ በ12 ማሽኖች ከመጋቢት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ዓረሙን የማስወገድ ስራ ማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ነው ያሉት።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በሃይቁ ላይ አሁን ያለውን እንቦጭ አረም ሽፋን በቴክኖሎጅ እና በሰው ጉልበት በመታገዝ ወደ 20 በመቶ ለመቀነስ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.