Fana: At a Speed of Life!

የኦፌኮ አመራራር አቶ በቀለ ገርባና የአቶ ጃዋር መሀመድ ጠባቂዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ አስክሬን በመቀማት እና ሁከት በመፍጠር ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ በቀለ ገርባና ሁለት ልጆቻቸውን እንዲሁም የአቶ ጃዋር ጠባቂዎች የሆኑ ዘጠኝ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ከእነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት በትናንትናው እለት ተሰይሞ ነበር።

ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር በተያያዘ መርማሪ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ወደ ተለያዩ አካበቢዎች ስልክ በመደወል ሁከት እንዲቀሰቀስና ነዋሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የመንግስት ደጋፊዎች ላይም ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ያስተላለፉበት የስልክ ልውውጥ በማስረጃ መልክ ማግኘቱን አስታውቋል።

ከዛም ባለፈ በአቶ በቀለ ገርባ ቤት ባደረገው ብረበራ ሁለት ሽጉጦች መገኘታቸውን እና ፍቃድ ይኑራቸው አይኑራቸው ገና እያጣራ መሆኑን መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል።

ሌላው በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ሁከት 140 ሚሊየን ብር እንደወደመባቸው የሚናገሩ ሁለት ግለሰቦች ማግኘቱንና ይህ የሆነውም አቶ በቀለ ገርባ ባስተላለፉት መልዕክት ነው ብሎ መርማሪ ፖሊስ በማመኑ ተጨማሪ የምረመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በቀጣይ ከሚሰራቸው ስራዎች ውስጥም ሸገር እና አንበሳ አውቶቢስ ላይ እንዲሁም ሌሎች የግል ንብረቶች ላይ የደረሱ ውድመቶችም እንደማስረጃ ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገውም አስታውቋል።

አቶ በቀለ ገርባ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የለኝም ለቅሶ ለመድረስ በአሸዋ ሜዳ ስሄድ መንገድ በመዘጋቱ ነው የተመለስኩት እና ወደ ኦሮሞ ባህል ማዕከል ያቀናሁት ቢሉም፤ መርማሪ ፖሊስ ግን አስክሬን በሃይል ቀምተው መስቀል አደባባይ ለ10 ቀናት አቆይተው ህዝብን በማስለቀስና ብጥብጥ ለመፍጠር አቅደው የፈጸሙት መሆኑን በምላሹ ጠቅሷል።

ከአቶ በቀለ ገርባ ሁለት ልጆች ጋር በተያያዘ መርማሪ ፖሊስ የአባታቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ሁከት ሲያነሳሱ ነው በቁጥጥር ስር ያዋልኳቸው ያለ ሲሆን፥ ጠበቆቻቸው ደግሞ ልጆቹ ለቅሶ ለመድረስ ከአባታቸው ጋር አብረው ስለተገኙ ብቻ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት ብሏል።

ከአቶ ጃዋር መሃመድ የግል ጠባቂዎች ጋር በተያያዘም፤ ከ10 ጠባቂዎቹ መካከል ዘጠኙ ቀርበዋል፤ አንደኛው በኮቪድ-19 ተጠርጥሮ ወደ ለይቶ ማቆያ በመወሰዱ ችሎት አልቀረበም።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ የሃኪመ ማስረጃ እንዲቀርብ አዟል፤ ከዘጠኙ ግለሰቦች ጋር በተያያዘ ዘጠኝ መገናኛ ሬዲዮ፣ ዘጠኝ ሽጉጥና አስር ክላሽ መገኘቱን መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል።

በነዚሁ ጠባቂዎች ምክንያት አስክሬን ይዘው ወደ ኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት በገቡ ጊዜ የአንድ ልዩ ሃይል ህይወት ማለፉንና ሌሎች ሶስት ልዩ ሃይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል፤ በዚህም የተነሳ በአካበቢው ሁከት መፈጠሩን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።

በኤግዚቢትነት ከተያዙት እቃዎች ውስጥ ወደማስረጃነት የሚቀየሩ ጉዳዮችን ለመመርመር ጊዜ እንደሚያስፈልገው ፖሊስ አስታውቋል።

ሰባት መርማሪዎች በተለያዩ የአሮሚያ ክልል አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸው የሰውና የንብረት ጉዳት መጠንን ለመመርመርና ማስረጃ ለመሰብሰብ በማቅናታቸው እነርሱ ይዘው የሚመለሱትንና ሌሎች ማስረጃዎችን ለማሰባሰበ 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።

ጉዳዮን የተመለከተው ችሎትም የተጠርጣሪዎችን መቃወሚያ አድምጦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል አይገባም በሚለው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐምሌ 9 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪከ አዱኛ

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.