Fana: At a Speed of Life!

የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን መፍጠር ይገባል­- ኢ/ር ታከለ ኡማ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን መፍጠር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የስራ ኃላፊዎችና እና የቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጆች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በከተማዋ ከተለያዩ ምንጮች የሚሰበሰበው ገቢ በትክክለኛው መጠንና ዘመናዊ በሆነ መልኩ መሰብሰብ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

በከተማ አስተዳደሩ የሚሰበሰቡ ታክሥና ታክሥ ያልሆኑ ገቢዎች ዘመናዊ መልክ እንዲይዙ እንዲሁም የማዘጋጃ ቤታዊ እና ሌሎች ከአገልግሎት በሚሠበሠቡ ገቢዎች ላይ የሚታየውን ክፍተት በማቃለል ከተለያዩ ዘርፎች የሚሠበሠበው ገቢ ለከተማዋ ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ እንዲያድግ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

በውይይቱ ላይም ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ ከተለያዩ ዘርፎች የሚሰበሰበው ገቢ በጥብቅ ዲስፒሊን እንዲመራ፤ ገቢው የሚሰበሰብበት መንገድ የዜጎች አቅም ያገናዘበ እንዲሁም ከተማዋ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ ማስቻልን ማእከል ያደረገ እንዳለበት ገልፀዋል።

የከተማዋን ገቢ ለማሳደግም የተለያዩ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን መፍጠርም ይገባል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የታክስ አሰባሰብ ሂደቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አስታውቅዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.