Fana: At a Speed of Life!

የከተራ በዓል ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የከተራ በዓል በዛሬው ዕለት በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ ውሏል።

በመላ ሀገሪቱ ታቦታት ከአድባራት ወጥተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ወርደዋል።

ታቦታት ወደ ማደሪያቸው ጥምቀተ ባህር ከደረሱ በኋላም አዳራቸውን በዚያው የሚያደርጉ ሲሆን፥ በካህናትና ዲያቆናት ዝማሬና ሌሎች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ይከወናሉ።

ነገ በማግስቱ ደግሞ የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች የሚከበር ይሆናል።

በዓሉ በአዲስ አበባ በጃን ሜዳ በአቅራቢያ የሚገኙ የ11 ደብራትና ገዳማት ታቦታት የጥምቀት በዓልን በጋራ የሚያከብሩ ሲሆን፥ ዛሬ ከቀኑ ስምንተ ሰዓት ጀመሮ ከአድባራትና ገዳማት ጉዞ በመጀመር ታቦታቱ ምሽት ላይ ጃን ሜዳ አርፈዋል።

በአዲስ አበባ ካሉ የታቦታት ማደሪያ መካከል አንዱ በሆነው ወደ ጃንሜዳ ታቦታት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በበርካታ ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ታጅበው ተጉዘዋል።

በጎንደር ከተማ ደግሞ የእምነቱ ተከታዮችን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ጎብኝዎች በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርዓት መከበር የጀመረ ሲሆን፥ በአሁኑ ሰዓት ታቦታት ከመንበራቸው ወደ ማደሪያቸው ተጉዘዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ፣ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በጎንደር ታድመዋል።

በትግራይ ክልልም መቐለ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እየተከበረ ሲሆን፥ በተለይም በማይጨው ከተማ በደማቅ ስነ ስርዓት ተከብሯል።

በኦሮሚያ ክልልም በተለያዩ ከተሞች ሀይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ታቦታት ከአድባራት ወጥተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ በመውረድ ተከብሯል።

በሀዋሳ ከተማም የከተራ በዓል በመላው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

በከተማዋ ታቦታት ከስምንት አብያተ ክርስቲያናት ተነስተው በካሕናትና በምዕመናን ታጅበው ወደ ማደሪያቸው አምርተዋል።

በድሬዳዋ ከተማም ታቦታት ከአድባራት ወጥተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ወርደዋል።

የከተራና የጥምቀት በዓላት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት መካከል ይጠቀሳሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.