Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1 ሺህ 495ኛው የመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1 ሺህ 495ኛው የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ሙስሊሞች በዓሉን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጎዱና ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ እንዲያከብሩት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው የዘንድሮው የመውሊድ በዓል መልካም የሆኑ ነገሮች በተመዘገቡበት ወቅት የሚከበር ቢሆንም ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች የተከሰቱበት ወቅት መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ህዝበ ሙስሊሙ የሚጠበቅበትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጣ የጠበቀ አደራዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ብለዋል።

መላው የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች የመውሊድ በዓል አከባበር ስርዓቶችን ስትከውኑ ራሳችሁን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመጠበቅ እና በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ ጭምር መሆን አለበትም ብለዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ 1 ሺህ 495ኛውን የነቢዩ መሀመድ የልደት በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት መላው የሀገሪቱ እና የክልሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ይህንን ታላቅ በዓል ሲያከብሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴቶችን በማጎልበት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የመውሊድ በዓል ሲያከብር በሀይማኖት አባቶች የተላለፈውን የጥንቃቄ መልዕክት መተግበር ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በከተማዋ፣ በሀገሪቱ እና በዓለም ዙሪያ ለሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በመሉ እንኳን ለ1 ሺህ 495ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) መውሊድ በዓል በሰላም አደረሳቹህ ብለዋል።

በዓሉ የሰላም ፣የፍቅር እና የደስታ እንዲሆንላቹህ እመኛለሁም ነው ያሉት ባስተላለፉት መልዕክት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.