Fana: At a Speed of Life!

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በምጣኔ-ሀብት ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ጫና የሚቀንሱ የፖሊሲ ውሳኔዎች ተላልፏል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ምጣኔ-ሃብት ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ ያስችላሉ ያላቸውን የተለያዩ የፖሊሲ ውሳኔዎች ማሳለፉን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ገለጹ።

ውሳኔዎቹ ከውዝፍ የግብር እዳ ጋር የተገናኙ የዜጎችን ኑሮ መታደግ ላይ ያተኮሩ ናቸው ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ እንዳሉት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግስትና ህብረተሰቡ ርብርብ እያደረገ ነው።

መንግስት ቀደም ሲል ወረርሽኙ በምጣኔ-ሃብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በተለይ በወጪ ንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት ባንኮች አስፈላጊውን የብድር ሽግሽግና ተጨማሪ ብድር እንዲያቀርቡ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

”በአሁኑ ጊዜም ለወረርሽኙ ተጋላጭ  የሆኑ ተቋማት ጉዳታቸው እየሰፋ እንዳይሄድ ተጨማሪ የኢኮኖሚ እርጃዎችን መውሰድ አስልፈጓል” ነው ያሉት።

የኢኮኖሚውን መቀዛቀዝ ተከትሎ በቢዝነስ ተቋማት ላይ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለ 15 ነጥብ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም ገልጸዋል።

በዚህ መሰረት የፌዴራል መንግስት ከ1997 እስከ 2007 ዓ.ም ውዝፍ የግብር ዕዳ ላለባቸው የቢዝነስ ተቋማት ስረዛ አድርጓል።

ግብር ከፍለው የኦዲት ግኝት የተገኘባቸው ተቋማትም ውዝፍ የኦዲት ግኝታቸውን ውሳኔው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ  በአንድ ወር ውስጥ ፍሬ ግብሩን በሚቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ከፍለው እንዲጨርሱ ተወስኗል።

”የፍሬ ግብራቸውን 25 በመቶ በመጀመሪያ በመክፈል ቀሪውን በተሰጣቸው ጊዜ ለሚከፍሉ ተቋማት የግብር ቅጣትና ወለድ ይነሳላቸዋል” ብለዋል።

ሙሉ የፍሬ ግብሩን በአንድ ጊዜ የሚከፍሉ ተቋማትም የአስር በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ውሳኔውን ለማስፈጸም ገንዘብ ሚኒስቴርና የገቢዎች ሚኒስቴር ዝርዝር መመሪያ እያዘጋጁ መሆኑን ጠቁዋል።

”ከኦዲት ግኝትና ከውዝፍ ጋር ተያይዞ በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ተቋማትም ፍሬ ግብራቸውን ከፍለው ከክርክር መውጣት እንደሚችሉና ይህ ግን በግብር ከፋዮቹ ፈቃደኝነት ሚሰወሰን ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ ለተከራዮቻቸው የቤት ኪራይ እፎይታ ለሰጡ ግለሰቦችና ተቋማት የኪራይ ገቢ ግብር ስረዛ አድርጓል።

”ይህ ውሳኔ ተቋማቱን ማመስገንና ሌሎችን ለማበረታታት ነው” ብለዋል።

በገቢ መቀዛቀዝ ምክንያት ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል ያልቻሉ ተቋማትን ለማገዝም ተቋማቱ ለሰራተኞች የሚከፍሉትን የአራት ወር የደመወዝ ግብር አስቀርተው ለሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ እንዲያውሉት ውሳኔ ተላልፏል።

የፖሊሲ ውሳኔው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ጤና ተቋማትና የተለያዩ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ያጠቃልላል ነው የተባለው።

መንግስት ይሄን የወሰነው በወረርሽኙ ምክንያት የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ለማነቃቃት ተቋማቱ ሰራተኞቻቸውን ሳይበትኑ ስራቸውን መስራት እንዲችሉ ለማገዝ እንደሆነም ዶክተር ኢዮብ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.