Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ቤቶች የዕውቀት ማዕድ በመሆናቸው የመማር ማስተማር ሂደቱን መቀጠል ወሳኝ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የመማር ማስተማር ሂደት መጀመሩን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት በመልካም ስነልቦና እና በዕውቀት የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ዛሬ በዘርፉ ላይ መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካጋጠመ በኋላ ዓለም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካ ጫና ስር ወድቃ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደቱም በዚሁ ወረርሽኝ ተፅዕኖ ስር ወድቆ መቆየቱን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቫይረሱ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሲባል ትምህርት ቤቶች ተዘግተው መቆየታቸን አውስተዋል፡፡

ወረርሽኙን በመከላከል ትምህርት ማስቀጠሉ ሀገር የሚረከብ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም ገልፀዋል፡፡

ተማሪዎችና መምህራን ተወዳጅ የዕውቀት መገበያያ ስፍራ የሆነውን ትምህርት ቤቶቻቸውን ርቀው መቆየታቸውን ጠቅሰው፥ ይህም የስነ ልቦና ጫናው ከባድ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

መንግስት ኮሮና ቫይረስ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እንቅስቃሴውን በመገደብ ስርጭቱ እንዳይስፋፋ ሲሰራ የቆየበት መንገድ ውጤታማ እንደነበረም ገልፀዋል፡፡

የዓለም ሀገራት ወደ መደበኛ ህይወት እንቅስቃሴ እየተመለሱ በመሆኑ ትምህርትና ሌሎች ስራዎች በጥንቃቄ እንዲከወኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወስኗልም ነው ያሉት፡፡

በዚሁ መሰረት በቂ ዝግጅት በማድረግ፣ ለቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት በማይሆን መንገድ በጥንቃቄ የመማር ማስተማር ሂደቱን መቀጠሉ አስፈላጊ ስለሆነ ለነገ በመልካም ስነ ልቦና፣ ዕውቀትና ብቃት የታነፀ ትውልድ እንዲኖር ትምህርት ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ተማሪዎችና መምህራን ወደ ትምህርት ቤት በመመላሳቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

መንግስት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመከላከያ ቁሳቁሶች ለተማሪዎች እንዲደርሱ ተሰርቷልም ነው ያሉት፡፡

የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለትምህርት ቤቶች ከማዳረስ በተጨማሪ መንግስት ተጨማሪ የትምህርት ክፍሎችን ግንባታ ሲያካሂድ መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የመማር ማስተማሩ ስራም በተገቢው መንገድ እንዲሳለጥ የትምህርት ተቋማት አካባቢ ሰላማዊ እንዲሆኑ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ከመንግስት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የትምህርት ተቋማት ተልዕኮና ራዕይ ሀገር የሚያሻግር፣ ብቃትና ክህሎት ያለው ትውልድ ማፍራት ስለሆነ የተማሪዎችን ቤተሰብ ጨምሮ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል አቶ ሽመልስ አብዲሳ፡፡

ትምህርት ቤቶች የዕውቀትና ፈጠራ መቅሰሚያ ስለሆኑ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንደሚያስፈልግ በመጥቀስም፥ ለዚህም የተማሪዎች ቤተሰብ፣ ነዋሪዎች፣ የመንግስትና የፀጥታ አካላት ሁሉ የነቃ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.