Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ዙሪያ የሚሠራ ኮሚቴ ተቋቋመ

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 17፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ዙሪያ የሚሠራ ኮሚቴ መቋቋሙን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ዙሪያ በዘርፉ የተሰማሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚሳተፉበትና የበኩላቸውን ድጋፍ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በዚህም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በዘርፉ የተሠማሩ የልማት አጋሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበራት፣ የግል ባለሀብቶች፣ የጥበብና የሚዲያ ባለሙያዎች በሚሳተፉበትና የበኩላቸውን ድጋፍ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ በሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች አካባቢ ስለተለዩ ፍላጎቶች ለውይይቱ ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

ከውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ጋር በተያያዘም በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል።

የተቋቋመው ኮሚቴም ከአዲስ አበባ አስተዳደርና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከልማት አጋራት፣ በዘርፉ ከተሰማሩ የግል ባለሀብቶችና ሌሎች ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ እስካሁን ባሉትና ወደፊት በሚቋቋሙት ለይቶ ማቆያዎችን ሊኖሩ የሚችሉ ፍላጎቶችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በሚኒስቴሩ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ ፥ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የሚያስችል ሃብት ለማሰባሰብ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

አንዳንዶቹ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከየተቋማቱ የሚደረገው ድጋፍ በዓይነትና በገንዘብ እስከ ነገ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.