Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣይ ቀናትም የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ-  ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ በቀጣይ ቀናትም የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ሴክሬታሪያትና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሚኒስትሮች ኮሚቴ በዛሬው እለት ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ በመደበኛ ስብሰባው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያላቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች የተመለከተ ሲሆን ባለፉት ሁለት ቀናት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንም መገምገሙን ገልፀዋል።

በዚህ መሰረት ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ቀናት የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱንና አዳዲስ ባህሪያትም እየተስተዋሉ እንደሚገኝ ኮሚቴው ተወያይቷል ብለዋል።

በተለይ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ንክኪ ያላደረጉ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ኮሚቴው ተመልክቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሰዎች ጎላ ያለ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት ሳያሳዩ በምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው በመታወቁ ስርጭቱን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው የሚኒስትሮች ኮሚቴ መገምገሙን ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገልፀዋል።

ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዞ ያለውን የወረርሽኝ ስርጭት የሚኒስትሮች ኮሚቴዉ በዝርዝር ከገመገመ በኋል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከፀጥታ አካላት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን ተጨማሪ ግብረ ሃይል በማቋቋም ባለፉት 2 ቀናት በርካታ የዝግጅት ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፥ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉም ብለዋል።

በተፈጠረው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በውጭ ሀገራት በተለይም በመካካለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎቻችን ወደ ሀገር ለመመለስ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት፥ ቤሩት የሚገኙ 669 ዜጎቻችንን ለመቀበል ዝግጅት አጠናቀናል ብለዋል፡፡

በዛሬ ዕለት ብቻ 333 ዜጎች ወደ ሀገራቸዉ የገቡ ሲሆን፥ ቅዳሜ ግንቦት 22 ቀን 2012 ዓም ደግሞ 333 ዜጎች ወደ ይገባሉ ብለዋል።

ከዚህ ቀደም መንግስት በገባዉ ቃል መሰረት በቀጣይም በችግር ውስጥ ያሉ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዜጎቻችንን የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ክብርት ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

ሌላው የሚኒስትሮች ኮሚቴ የተወያየው ከድንበር አካባቢ ጋር ተያይዞ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ ሲሆን፥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያመጡ መሆኑን አይቷል።

ህብረተሰቡ በድንበር በኩል ተደብቀው የሚገቡ ዜጎችን በማጋለጡ ሂደት ከፀጥታ አካላት ጋር ያለው መተባበር ጥሩ ጅምር ላይ እንዳለ ኮሚቴው ገምግሟል።

በድንበር አካባቢ የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን በማዘጋጀት በተለይ በመተማ በኩል አቋርጠው የሚገቡ ዜጎችን ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን የማጠናከርና የቁጥጥር ሂደቱን የማጥበቅ ስራዎች አሁንም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ የድንበር አቋራጭ ሾፌሮች ሁኔታንም የተመለከተ ሲሆን፥ በቀጣይ የአሽከርካሪዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ጤንነት ለመጠበቅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ሴክሬታሪያትና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ወይዘሮ መኩፈሪሃት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክትም፥ አሁንም የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ በቀጣይ ቀናትም የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ።

ከዚህ በሻገር ግን ህብረተሰቡ እራሱን፣ ቤተሰቡን፣ አካባቢውንና ሀገሩን እንዲጠብቅ ከአደራ ጭምር ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.