Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣የካቲት 10፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ባለድርሻ አካላትና የክልል መስተዳድሮች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንስቲትዩቱን የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ በሽታ ወደ ሀገር እንዳይገባ እየተደረገ ያለውን የመከላከል ስራን አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ገለጻ አድርገዋል።

በዚህ ወቅትም ባለድርሻ አካላትና የክልል መስተዳድሮች አስፈላጊውን ድጋፍና ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በሽታው ከጉንፋን ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በ14 ቀናት ውስጥ ሳል፣ ንጥሻ፣ የትንፋሽ ማጠርና የጉረሮ ህመም ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን ÷ይህም በሽታው በፍጥነት እንዲዛመት ያደርጋል ሲሉ ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

ይህም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገሮች አስጊ በመሆኑ አስፈላጊውን ትኩረት መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ቫይረሱ ወደ ሀገር እንዳይገባ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት እና ከ150 በላይ ባለሙያዎች ያካተተ የድንገተኛ ማዕከል በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ሆኖም አንዳንድ ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ለምርመራ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የፀጥታው ሀይል ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ዶክተር ኤባ ገልፀዋል፡፡

በሌላም በኩል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚሰሩ ስራዎች በመኖራቸው መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አለበትም ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም ቦሌ ጨፋ ኢቦላ ማዕከል፣ የካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታልና ቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቁ መሆናቸውም ጠቁመው ነገር ግን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚሸፍን አገልግሎት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በየካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ያለውን ዝግጁነት ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን ከጉብኝቱ ገለፃ በተጨማሪ ያሏቸውን ሃሳቦች በማንሳት ውይይት ማካሄዱን ከህዝብ ተወካዮች ምር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.