Fana: At a Speed of Life!

የወላይታ ፣ ጋሞና ጎፋ ህዝቦች እያጋጠሙ ያሉ የግጭት ሙከራዎችን በተደጋጋሚ በመከላከል የሰላም ፈላጊነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን የዞኖቹ አመራሮች ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 27፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ፣ ጋሞና ጎፋ ህዝቦች እያጋጠሙ ያሉ የግጭት ሙከራዎችን በተደጋጋሚ በመከላከል የሰላም ፈላጊነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን የዞኖቹ አመራሮች ገለፁ በደቡብ ክልል የወላይታ ፣ የጋሞና የጎፋ ዞኖች አመራሮች እንዲሁም የዞኖቹ ተወላጅ የሆኑ የፌደራልና ፣ የአዲስ አበባ እና የክልሉ አመራሮች በተገኙበት ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረውን የጋራ ኮነፈረንስ መጠናቀቅ አስመልክቶ መግለጫ ወጥቷል፡፡

በመግለጫው ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች ወደ እርስ በእርስ መጠራጠር እና ወደ ግጭት እንዲገቡ የመገፋፋት ቀስቀሳዎችና ሙከራዎች በዞኖች ሲደረጉ እንደነበር እና አሁንም መቀጠሉን በውይይቱ መነሳቱን መግለጫው አመልክቷል። በዚህም ውስጥ አመራሩ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ያለውና በብዙ ችግሮች ውስጥም ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ የቆየበት እንደነበር የተገመገመ ሲሆን በቀጣይም እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም መግባባት ላይ በመድረስ ኮንፈርነሱን ማጠናቀቅ መቻሉ ተገልጿል፡፡ የዞኖቹ ህዝቦችም እያጋጠሙ ያሉ የግጭት ሙከራዎችን በተደጋጋሚ በማክሸፍ ሰላም ፈላጊነቱን በተግባር እያሳየ መዝለቅ መቻሉን ተነስቷል፡፡

ነገር ግን አሁንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተነሱ እና መንግስት ምላሽ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰባቸው ያሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ሰበብ በማድረግ በህዝቦች መሃከል ግጭት ለማስነሳት የሚደረጉ የተለያየ ሙከራዎች አሁንም መቀጠላቸው በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በዚህ መድረክ ተሳታፊ የሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የዞኖቹ ተወላጅ አመራሮች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በግልፅነት ከችግር ሊያወጣ የሚችል ውይይት ማካሄድ መቻላቸው ተጠቁሟል።

በመሆኑም የዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛው ማእከል ህዝቡን ከፊት ሆኖ ወደ ብልፅግና ጎዳና እንዲያመራ የተመደበው አመራር በመሆኑ ራሱን በሚገባ በመፈተሸ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የፈጠራቸውን ችግሮች ለማረም በፍጥነት ለመንቀሳቀስም ተግባብቷል፡፡ ዘላቂና ቋሚ የሆነው የህዝቦች ግንኙነት ከየትኛውም ጥያቄ በላይ በመሆኑ የህዝቦችን ግንኙነትና አብሮነት ማጠናከር ፣ የህዝቦችን ግንኙነትና አብሮነት ማጠናከር ፣ የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ እና የአካባቢውን ሰላም የማስጠበቅ ጉዳይ የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን በአግባቡ መረዳት እደሚገባ ተጠቁሟል።

አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ከውስጥም ከውጪም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ላይ የማያወላዳ እርምጃ እየወሰዱ ለመሄድና ህግ የበላይነትን ለማስፈን ቁርጠኛ አቋ መወሰዱን እንዲሁም የሰላም ማስከበሩ በፍጥነት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ዞኖቹ ተናበው እና ተደጋግፈው ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

እንዲሁም እስካሁን የነበረው የሚዲያ አጠቃቀም  ታርሞ መላው መዋቅሩና ህዝቡ ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ፤  የህዝቦችን አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ ለማረም እና ሁሉንም ልዩነትን ሊያሰፉ የሚችሉ ጉዳዮችን በጋራ  ለመፍታት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.