Fana: At a Speed of Life!

የወረታ ደረቅ ወደብ በሚቀጥለው ሳምንት ይመረቃል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የወረታ ደረቅ ወደብ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሚቀጥለው ሳምንት ይመረቃል።

የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ ስፈጻሚ አቶ እውነቱ ታዬ እንደገለጹት፥ የወደብ ልማቱ ሀገሪቱ ያላትን የደረቅ ወደብ ቁጥር ወደ ስምንት ከፍ ያደርገዋል።

በአጠቃላይ 25 ሄክታር መሬት ሽፋን የሚኖረው የወረታ ደረቅ ወደብ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሶስት ሄክታር መሬት ግንባታ ተጠናቆ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመረቅ ተናግረዋል።

ቀሪው ሔክታር በቀጣዮቹ ዓመታት የሚለማ ሲሆን፥ ሀገሪቱ ያላትን የደረቅ ወደብ የማስተናገድ አቅም በስምንት እጥፍ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የወረታ ደረቅ ወደብ ለሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢ የወጪና ገቢ ንግድን ለማስተናገድ የሚያገለግል ሲሆን፥ አገልግሎት ፈላጊው የነበረበትን እንግልት ይቀንሳል ተብሏል።

በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የወረታ ደረቅ ወደብ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።

ደረቅ ወደቡ ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለአካባቢው የንግድ ማህበረሰብ ለማቅረብም አገልግሎት ይሰጣል።

ይህም የመልቲ ሞዳል አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ይባክን የነበረውን የጊዜና ገንዘብ ወጪ እንደሚቀንስ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የንግድና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ የደረቅ ወደብ ልማት በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጊዜ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ በግንባታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ የመቐሌ ደረቅ ወደብ ማስተር ፕላንን በዚህ አመት በማጠናቀቅ በቀጣይ አመት ግንባታው እንደሚጀመር አንስተዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብን ዋና ማዕከል ለማድረግ 100 ሚሊየን ብር ተመድቦ እየለማ ሲሆን፥ ከአለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተጨማሪ 30 ሔክታር ለማልማት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ በጂቡቲ ለወደብ ኪራይ ይወጣ የነበረውን ገንዘብና እንግልትን እንዲቀንስ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

እያንዳንዱ አስመጪ ያመጣውን ኮንቴነር በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ከደረቅ ወደቡ ማንሳት የሚጠበቅበት ቢሆንም ኮንቴነሮች በደረቅ ወደብ ለዓመታት እንደማይነሱ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆ፥ን ችግሩ በመንግስት ተቋማት ላይ በስፋት ይስተዋላል።

በአሁኑ ወቅት ረዥም ጊዜ የቆዩ ኮንቴነሮች እንዲወጡ ግፊት እየተደረገ ነው መሆኑንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ሀገር በመሆኗ ለወደብ ኪራይ የሚወጣውን በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ለማስቀረት ባለፉት 11 አመታት የደረቅ ወደብ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጋለች።

የወደብ መቋቋም ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ለንግድና ኢንቨስትመንት መነቃቃት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

ሞጆ፣ ቃሊቲ፣ ገላን ሙሉ በሙሉ አግልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ደረቅ ወደቦች ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.