የወራቤ ሆስፒታል የጥናት እና ምርምር ማዕከል እንዲሆን እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣የካቲት 17፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)የወራቤ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጥናት እና ምርምር ማእከል እንዲሆን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል ሽፋ ÷ በሆስፒታሉ የልብ፣የካንሰር እና የኩላሊት ህክምናዎችን ለመጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ በቅርቡ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምናን መስጠት መጀመሩን የጠቆሙት ሃላፊው፥ ከዚህ በተጨማሪ ከአንገት በላይ ህክምና ፣ የአጥንት ህክምና፣ አጠቃላይ ቀዶ ህክምና፣ የስነ አዕምሮ እንዲሁም የህፃናት ህክምና በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሆስፒታሉን አሰራር በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።
በስልጤ ማህብረሰብ ወጭ በ 300 ሚሊየን ብር የተገነባው እና 5ኛ ዓመቱን የያዘው ሆስፒታሉ 584 አልጋዎችን መያዙ ተገልጿል፡፡
በሆስፒታሉ በየቀኑ ከ 700 በላይ ታካሚዎች የሚስተናገዱ ሲሆን÷ በሳምንት ከ90 በላይ ትላልቅ የቀዶ ጥገና ህክምናዎች የሚሰጡ መሆኑም ተመላክቷል።
በዙፋን ካሳሁን