Fana: At a Speed of Life!

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ አስፈላጊው ግብዓት ይሟላል- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት በሁሉም ወረዳዎች በሚፈለገው መንገድ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ አስፈላጊው ግብዓት እንደሚሟላ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የአዲስ አበባ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ምክር ቤት የምስረታ ጉባዔ መካሄዱን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የምስረታ ጉባዔው ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፌደራል ኢሚግሬሽን እና የዜግነት ወሣኝ ኩነት ኤጀንሲ አቶ ሙጂብ ጀማል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ምዝገባ ሙስናና የማጭበርበር ስራዎችን ለመከላከል፣ ለማህበራዊ ደህንነት አጠቃላይ የከተማዋን አገልግሎት ፍጥነት እና በትክክለኛው መረጃ ላይ ተመርኩዞ ውሣኔዎችን ለመስጠት እንዲሁም ስራዎችን በአግባቡ ለመከወን አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የምዝገባ አገልግሎቱ በሁሉም ወረዳዎች በሚፈለገው መንገድ የተቀላጠፈ እና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የከተማ  አስተዳደሩ ከግብዓት ጀምሮ አስፈላጊው ነገር እንደሚሟላም አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ መቋቋምም መረጃዎችን በማጥራትና ተደራሽ የማድረግ ከዛም በሚገኘው ውጤት ስራዎችን ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ መሆን እንዲችሉ ለማስቻል ስለሆነ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በተግባር ማሳየት ይኖርበታል ብለዋል።

ነዋሪዎች የግል ሰነዳቸውን የራሣቸው ትልቅ ንብረት ሆኖ የማገልገሉን አስፈላጊነት የምክር ቤቱ አባላት ማስገንዘብ እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መጫ በበኩላቸው፥ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት በተለይ በመታወቂያ፣ በልደት እና የጋብቻ የሃሰተኛ የምስክር ወረቀት መበራከት፣ በአንድ ቤት ስም በርካታ መታወቂያ የማስወጣት ዝንባሌ እንደሚስተዋል ነው የገለጹት።

አዲሱ ዲጅታል የነዋሪዎች መታወቂያ በ96 ወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ያሉት ዶክተር ታከለ፥ ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የዲጅታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸውን እና እስካሁንም ለ140 ሺህ የዲጂታል መታወቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በጉባዔው በወሳኝ ኩነት አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሰራተኞች፣ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.