Fana: At a Speed of Life!

የወጪ ገቢ እንቅስቃሴ በኢ-ሰርቪስ አገልግሎት አማካኝነት በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የሀገር ውስጥና የድንበር ተሻገር የጭነት ትራንስፖርትን በማዘመን የሀገሪቱን የወጪ ገቢ እንቅስቃሴ ቀልጣፍ፣ ምቹና ተወዳዳሪ እንዲሆን በኢ ሰርቪስ አገልግሎት አማካኝነት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

ቀደም ሲል የነበረው የኢ-ሰርቪስ አግልግሎት በአብዛኛው ማኑዋል ላይ የተመረኮዘ ከመሆኑም ባሻገር፥ የተደራሽነት እና ማዕከላዊ ዳታ ሲስተም ችግር የነበረበት በመሆኑ በአዲስ የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ማሻሻያ መደረጉንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።

አዲሱ አገልግሎት የኢንተርኔት ዳታ ሲስተምን የሚጠቀም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፥ ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት ማህበራቶች እና ድርጅቶች የሚጠቀሙበትን አድራሻ በመክፈትና ከሲስተሙ ጋር በማገናኘት መጠቀም እንዲችሉ ያደርጋልም ነው የተባለው፡፡

የትራንስፖርት ኦፕሬተሮች፣ ስራ አስኪያጆች እና የቦርድ አባላት የዘርፉ ዋነኛ የባለድርሻ አካላት ስለሆኑ በሲስተሙ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ለትግበራውም የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መካሄዱንም ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አገልግሎት ፈላጊ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮች በተዘረጋው ሲስተም አማካኝነት አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶቻቸውን ስካን በማድረግና ሲስተሙ ላይ በመጫን በአዲስ መልክ በመመዝገብ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት ይችላሉም ተብሏል።

ለዚህም የጭነት ትራንስፖርት ማህበራት የማመልከቻ መስፈርቶች፣ የተሽከርካሪ ዝርዝር፣ ሊብሬ፣ ቃለ-ጉባኤ፣ የቢሮ ኪራይ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ ውስጠ ደንብ እና የአባላት የስምምነት ፊርማ አሟልተው መላክ ይኖርባቸዋል።

የግል ትራንስፖርት ድርጅቶች የተሽከርካሪ ዝርዝር፣ ሊብሬ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ የቢሮ ኪራይ ውል/ካርታ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

የአክሲዮን ማህበራትም የተሽከርካሪ ዝርዝር፣ ሊብሬ፣ ፈቃድ፣ የቢሮ ኪራይ ውል/ ካርታ፣ የንግድና የምዝገባ ፈቃድ፣ መመስረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መላክ እንዳለባቸውም ተጠቅሷል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተላከውን ማመልከቻ እና የአገልግሎት ጥያቄ ከተመለከተ በኋላ የሰነዶችን ትክክለኛነት አረጋግጦ ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፥ አገልግሎት ፈላጊዎች ክፍያ ለመፈፀምና ዋናውን ሰነድ ለማሳየት ብቻ ወደ ተቋሙ እንደሚመጡም ተነግሯል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.