Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ጽዮን ተክሉ ከዴንማርክ መንግስት የስደተኞች ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ፅዮን ተክሉ ከዴንማርክ መንግስት የስደተኞች ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ አንደርስ ታንግ ፈሪቦርን ጋር ተወያዩ፡፡

ሚኒስትር ዲኤታዋ ከልዩ መልዕክተኛው ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የዴንማርክ መንግስት ከዜጎች ጋር በተያያዘ ለሚያደርው ትብብርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታዋ አመስግነዋል።

በመካከለኛው ምስራቅና በሌሎች ሃገራት የሚኖሩ ዜጎች ከሚኖሩባቸው ሃገራት መንግስታት ጋር በመተባበር ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጠበቅና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሃገራቸው የሚመለሱ ዜጎችን ለማስመለስና መልሶ ለማቋቋም ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

መንግስት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከማስቀረት አንጻር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰፊ ጥረቶችን እያከናወነ መሆኑንም በውይይታቸው ጠቅሰዋል።

ልዩ መልዕክተኛው በበኩላቸው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከስር መሰረቱ ለማድረቅ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ተመላሽ ዜጎችን በተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ማብቃትና የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ ዴንማርክ አስፈላጊውን እገዛ እንደምታደርግ መናገራቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.